ኢትዮጵያ የምታስተናግደው ኮፕ 32 ጉባኤ ይዞት የሚመጣውን መልካም ዕድል አሟጦ ለመጠቀም እና ለጉባኤው ስኬታማነትም ሁሉም ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቅርበዋል።
ከንቲባዋ ዛሬ ማለዳ ከኡራኤል ብራስ፣ ቦሌ መድኃኔዓለም ጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የፒኮክ (ማዕከላዊ) ፓርክ ግንባታን መገምገማቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።
ይህ ኮሪደር በከተማዋ በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትን ለማስፋት የተጀመረ ዘጠነኛው ኮሪደር ሲሆን፣ አጠቃላይ 11.5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እና በውስጡ በርካታ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎችን የያዘ ነው
የግንባታው ሂደትም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል።
ከኮሪደሩ በተጨማሪም ለብዙ ዘመናት ተረስቶ የኖረ፣ ከሕዝብ ተወስዶ በግለሰቦች ያለአግባብ ተወሮ ለብዙ ብልሽት ተዳርጎ የኖረውን ታሪካዊውን የፒኮክ ወይም በጥንታዊ መጠሪያ ስሙ ማዕከላዊ ፓርክን ከወንዝ ዳርቻ ጋር አያይዘን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያለማነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በአዲስ አበባ ሌላኛው የስበት ማዕከል፣ ድንቅና ውብ ሥፍራ ሆኖ እየተገነባ ነው ብለዋል።
በተለይም የኮፕ 32 ጉባኤ በሚከናወንበት በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ አስቀድመው የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።
በዚህ አጋጣሚ የኮፕ 32 ጉባኤ ከዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የሚታደሙበት በመሆኑ፣ ይህ ጉባኤ በመዲናችን መዘጋጀቱ ከሀገር መልካም ገፅታ ግንባታ በተጨማሪ፤ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ትስስር እንዲሁም መሰል ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ወደ ሀገራችን በቀጣይነት ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ የሚፈጥር ስለሆነ ከመቼውም የበለጠ ትኩረት ይሻል።
በመሆኑም መላው የከተማችን ነዋሪዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጉባኤው ይዞት የሚመጣውን መልካም ዕድል አሟጦ እንድንጠቀም እና ለጉባኤው ስኬታማነትም ከወዲሁ ሁላችንም ዝግጅት እንድናደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁ።