Search

ኢትዮጵያ ተደንቃ የተጠቀመችባቸው ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች

ረቡዕ ታኅሣሥ 01, 2018 113

ያለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጠናከረበት እና ዕድገት የታየበት ነው። 

ለዚህም ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ የተወሰዱ እርምጃዎች እና የተገኙ ለውጦች ምክንያት ናቸው።

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተሠሩ ሥራዎች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ቅቡልነት ከፍ ካደረጉ ሥራዎች ተጠቃሽ ነው። ኢትዮጵያ  ለስንዴ ምርት የሰጠችው ትኩረት አንዱ ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት እና ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያስገኘ ነው።

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ኢትዮጵያ ከጣሊያን መንግሥት ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤን እንድታስተናግድም አስችሏል። 

በጉባኤው ከ4 ሺህ 700 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከዋናው ጉባኤ በተጓዳኝ ደግሞ 31 የተለያዩ የጎንዮሽ ሁነቶች ተካሂደዋል። ይህ ጉባኤ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችንም ይበልጥ ያጠናከረ እና ዓለም አቀፍ ቅቡልነቷንም የሳደገ ነው።

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ኢትዮጵያ ያስተናገደችው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤም ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል የተመዘገበበት ነበር።

በጉባኤው ከ20 ሺህ እስከ 25 ሺህ ሰዎች ተሳትፈውበታል፤ የ45 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማኅበራት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተውበታል። 

ከጉባኤው በተጓዳኝ ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነቷን አጠናክራበታለች። ይህ አህጉራዊ ጉባኤ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር አንዱ ማሳያ ነው።

ሌላው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራ የሠራችው ሥራ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል የተገኘበት ነው። ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ47 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተተክለዋል። ይህም ተመናምኖ 17.2 በመቶ የነበረውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን መጠን ወደ  23.6  በመቶ  አሳድጎታል።

ይህ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ ከጎረቤት ሀገራት አልፎ በሌሎች ሀገራትም ምሳሌ ሆኖ እየተሠራበት ነው። 

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እየሠራች ባለችው ጠንካራ ሥራ ምክንያትም የዓለም ሀገራት አምነውበት የCOP 32 ጉባኤን እንድታስተናግድ መርጠዋታል። ይህን ጉባኤ ማስተናገዷ አሁንም ይበልጥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን የሚያሳድግ እንደሚህን ይጠበቃል። 

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለመበልፀግ ያላት አቋምም ዲፕሎማሲያዊ ድል የተገኘበት ነው። ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከሕዳሴ ግድቧ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እያቀረበች መሆኗም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ያጠናከረ ነው።

ኢትዮጵያውያን በዓላማ ፅናት እና አንድነት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቃቸው ለኢኮናሚያዊ ዕድገት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት፣ የዓለም ሀገራትም ያደነቁት ነው። 

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለኢትዮጵያ አድኖቆታቸውን ችረዋል፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ  ግንኙነትም ተጠናክሯል። 

በአዲስ አበባ ከተማ እና በክልል ከተሞች እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማትም  የኢትዮጵያን ገፅታ የገነባ ነው። የሀገራት መሪዎች እና ዲፕሎማቶችም የኢትዮጵያን የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማትን አድንቀዋል። 

ከሰሞኑ ለአፍሪካ ሚዲያ አዋርድ ኢትዮጵያ የተገኙ እንግዶችም በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ በአግራሞት መመልከታቸውን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት  በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ እና ለኢኮኖሚያዊ  ዕድገት በሠራቻቸው ሥራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነት እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ ከፍ ለማለቱ ምክንያት ሆኖ ይነሣል። 

አስማረ ብርሃኑ 

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Ethiopia_rising #diplomacy