ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ለኢትዮጵያ - ጅቡቲ - ደቡብ ሱዳን የትራንስፖርት ኮሪደር ፕሮጀክት ምዕራፍ 2 ግንባታ የሚውል የ184 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ ለአዳማ - አዋሽ ምዕራፍ 2 የፍጥነት መንገድ ግንባታ የሚውል በጀት ለማቅረብ እንደሚረዳ ታውቋል።
የድጋፍ ስምምነቱ የተፈረመው በኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር አሌክስ ሙቢሩ (ዶ/ር) መካከል ነው።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ከአፍሪካ ቀንድ የትብብር ኢኒሼቲቭ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ለቀጣናው መረጋጋት፣ ትብብር እና ጥልቅ ውህደት ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር አሌክስ ሙቢሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባንኩ በተለያዩ ዘርፎች ስትራቴጂካዊ ትብብርን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በምታካሂዳቸው ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች የአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በሃብተሚካኤል ክፍሉ