ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ የተጠናከረበትና ዕድገት ያሳየበት ወቅት ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት፣ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት፣ የቀጣናውን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የተከናወኑ ሰፊ ጥረቶች፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይ የእዳ ጫና ያለባቸው ሀገራት የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ለዲፕሎማሲው መሻሻል የራሳቸው በጎ ተጽዕኖ አላቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ለዲፕሎማሲው ዕድገት ወሳኝ ድርሻ ነበራቸው።
የዓለም አቀፍ ዳያስፖራ ፎረም ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን አሻግሬ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተሻለ ተቀባይነት ያላት ሀገር እየሆነች መምጣቷን ተናግረዋል።
በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አስፈላጊ ሥልጠናዎችን ከወሰዱ በኋላ ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ትልቅ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ዲያስፖራዎች ዕውቀታቸውንም ሆነ ገንዘባቸውን መንግሥት በቀረፀው ፖሊሲ መሠረት ሀገራቸው ላይ በማፍሰስ በተለያየ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፖሊሲ ልማት ተመራማሪ ታፈሰ ማቲዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ የምትከተለው የዲፕሎማሲ መንገድ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሚዛኗን ሳትስት በሚገባት መንገድ እንድትጓዝ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሀገር አልፎ የአፍሪካንም ጥቅም ለማስጠበቅ እየተሠራ ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማ በመሆኑ የኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገጽታን ማሻሻል እንደተቻለም አንስተዋል።
ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ ሚዛኗን ጠብቃ ከዓለም ኃያላን ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ መቀጠሏ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑንም ነው ያመላከቱት።
ይህንን ዲፕሎማሲያዊ ድል አጠናክሮ መቀጠል እና በይበልጥ ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር እንደሚገባም ገልጸዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ