Search

ከተሞች የዕድገት ምሳሌ እንዲሆኑ ያስቻለው ሥራ

ዓርብ ታኅሣሥ 03, 2018 29

የመደመር መንግሥት ለከተሞች ዕድገት የሰጠው ትኩረት በርካታ ከተሞች ኢኮኖሚያቸው እንዲነቃቃ እና ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ አስችሏል፡፡
ከተሞች የቱሪስቶች መዳረሻ እንዲሆኑ እና ፀጋቸውን ለይተው እንዲያድጉ የተወሰደው እርምጃም ውጤት እያሳየ መሆኑን በርካቶች ይገልጻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማት ሥራው ከተሞችን በማዘመን ለኑሮ ምቹ፣ ጽዱ እና ውብ እንዲሆኑ በማድረግ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚቀይር መሰረት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት አስረድተዋል።
የመደመር መንግሥት ከተሞችን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እና አገልግሎቶችን ለማሳደግም ተጨባጭ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን መናገራቸው አይዘነጋም።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የመደመር መንግሥት ከተሞች በዘፈቀደ ሳይሆን በእቅድ እና በሥርዓት መመራት አለባቸው የሚለው እሳቤ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
በገጠር እና በከተማ ያለውን የዘመናዊ አኗኗር ልዩነት ማጥበብ እንዲሁም ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር እንደተቻለም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ከተሞች ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ምሳሌ መሆን ችለዋል ይላሉ፡፡
ከለውጡ በፊት ለከተሞች እድገት ትኩረት ባለመሰጠቱ፣ ከተሞች በሚገባቸው መጠን እንዳያድጉ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለይም ቀደም ባለው ጊዜ የግሉ ዘርፍ በቤት ልማት አቅርቦት ላይ በስፋት ተሳታፊ እንዳልነበረ ጠቁመው፤ የመደመር መንግሥት ግን የግሉን ዘርፍ ባሳተፈ መንገድ የቤት አቅርቦት ላይ በስፋት እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
ከተሞች የተለያዩ ማንነቶች፣ እሳቤዎች፣ ዕውቀት፣ ካፒታል እና ሀብት የሚንሸራሸሩባቸው መሆን እንዳለባቸው የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የመደመር መንግሥት ከተሞች ለሁሉም ዜጋ ምቹ መኖሪያ መሆን አለባቸው የሚል እሳቤን ይዞ የመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከተሞችን ወደ ጎን የማስፋት እንጂ ዕድገታቸው ላይ ብዙም አልተሰራም ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁን ላይ ግን ያ አሰራር መቀየሩንና ስሉጥ ከተሞችን (ስማርት ሲቲን) ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከተሞች ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ እንዳይሆኑ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ከተማ ሰፊ አረንጓዴያማ ቦታዎች እና ምቹ መናፈሻዎች ያልነበሯት፣ የታፈነች ከተማ እንደነበረች ያስታወሱ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን አዲስ አበባን የሚመጥኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
የነበሩ ጠባብ መንገዶችን በማስፋት እና የትራንስፖርት ተርሚናል በመገንባት የተሳለጠ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲኖር ማስቻሉንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
 
በሜሮን ንብረት