የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከ520 ሺህ በላይ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከተረጂነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር ችሏል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች ዛሬ ማለዳ በአዲስ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች፣ አራት G+4 የማምረቻ እና መሸጫ ህንፃዎችን ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) ፕሮግራም ታቅፈው ለነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች አስረክበዋል።
በከተማችን እየተተገበሩ ካሉ የዜሮ ግብ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ተረጂነት እና ልመናን ዜሮ ማድረግ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በዛሬው ዕለትም 976 አንቀሳቃሾችን በ292 ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት የማምረቻ እና መሸጫ ቦታ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁ በማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ህይወት በመለወጥና ከድህነት በማውጣት ኑሯቸውን በዘላቂነት ለመምራት እንዲችሉ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፥ ተጠቃሚዎች የተፈጠረላቸውን የሥራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሆነው ከተረጂነት ወደ አምራችነት በመሸጋገራቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ ያስረከብናችሁ የመስሪያ ቦታ ነገ እህቶቻችሁ፣ ወደፊትም ወንድሞችና ልጆቻችሁ ተረክበው የሚሰሩበት መሆኑን ተገንዝባችሁ በኃላፊነት ልትጠቀሙበት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።