መገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ያረፈበት ቦታ 870 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ 17 ሺህ ሔክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ይኖረዋል።
ከተጀመረ 15 ዓመታት ያስቆጠረው ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች እየተጓተተ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አልቻለም።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።
ፕሮጀክቱን በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ግንባታው በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ መሆኑን፣ ግንባታውን ካለፈው ዓመት ጀምሮ እያከናወነ የሚገኘው ሀገር በቀሉ ኮንትራክተር ቤአኤካ አስታውቋል።
በተለይም ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚረዱ መሰረታዊ የግንባታ ምዕራፎችን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉ ነው የተመላከተው።
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ግንባታ 77 በመቶ መድረሱም ተጠቅሷል። ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅም ለ24 ሰዓት የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለጎንደር እና በጎንደር ዙሪያ ለሚገኙ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል።
በአባዲ ወይናይ