በተያዘው ዓመት 12 ሚሊዮን አርሶና አርብቶ አደሮች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለመመዝገብ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በግብርናው ዘርፍ መተግበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ አቶ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ በዚሁ ወቅት፤ የአርሶ እና አርብቶ አደሩን የግብዓትና የፋይናንስ ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት ለማቅረብ በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት መጨረሻ እንደሀገር ይመዘገባል ተብሎ ከታቀደው 90 ሚሊዮን የፋይዳ መታወቂያ 12 ሚሊዮኑ የአርሶ እና አርብቶ አደሮች ድርሻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የግብርና ተዋናዩ ማህበረሰብ የፋይዳ መታወቂያ መመዝገቡ በቂ መረጃ ስለሚያደራጅ ለአበዳሪዎች ዋስትና እንደሚሆንም አብራርተዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ የአርሶ እና አርብቶ አደሩን የወደፊት ብልፅግና የሚወስን በመሆኑ ሁሉም መዋቅር ምዝገባውን እንዲያስተባብር ለክልሎች አሳስበዋል።
የግብርናው ዘርፍ የዲጂታል መረጃ ምዝገባ ለግብርና ዘርፍ ሽግግር ቁልፍ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
በባዬ ሙላት
#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #Fayda #NationalID