Search

በንግድ እና ኢንቨስትመንት ታጅቦ ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና የሕንድ ወዳጅነት

ማክሰኞ ታኅሣሥ 07, 2018 444

የኢትዮጵ እና የሕንድ ታሪካዊ ግኑኝት ሁለት ሺህ ዓመታትን ወደ ኋላ የሚወስድ፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተው ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነታቸው ደግሞ 70 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።

የጥንቱን ዘመን በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ታሪካዊ የንግድ ግኑኝነት ስንመለከት በአክሱም ዘመነ መንግሥት በአዱሊስ ወደብ በኩል የሕንድ ነጋዴዎች የጨርቃ ጨርቅ፣ የወርቅ፣ የቅመማ ቅመም እንዲሁም የዝሆን ጥርስ ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት የንግድ ሥራቸውን ያቀላጥፉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ።

ዘመናትን በዘለቀው የኢትዮጵያ እና የሕንድ ታሪካዊ ግኑኝነት ውስጥ ኢትዮጵያን ለመውረር የቋመጡ የአወሮፓ ቅኝ ገዢዎች ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ለማድረግ በተደረገው የትግል ሂደት ውስጥ ሕንድ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ ፍትሐዊ አጋሪነቷን ያረጋገጠች ሀገር መሆኗን ታሪክ ይመሰክራል።

የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግኑኝነት እያደገ በመምጣቱ ምክንያትም እ.አ.አ በ1950 ወደ መደበኛ ዲፕሎማሲያ ግኑኝነት እንዲሸጋገር ተደርጓል።

ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝት ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ በንግድ እና ኢንቨስትመንት እየተጠናከረ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል።

ከ650 በላይ የሕንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)፣ በማዕድን፣ ኢነርጂ እና መሰል ዘርፎች ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሙዓለ ንዋይ በማፍሰስ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትርጉም ያለው ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

ሕንድ የኢትዮጵያ ቁልፍ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አጋር ከመሆን በሻገር በትምህርት እና በጤና፣ በውኃ አስተዳደር እና በፋይናንስ ዘርፎች ዘመናዊ የሆነ ተቋማዊ አሠራር በመዘርጋት ሂደት ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር እየሠራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማካሄዷ በርካታ የውጭ ሀገር ኩባንያዎችን ቀልብ የሳበ ጉዳይ ነው። የሕንድ ኩባንያዎች በፊት ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ የነበሩ እና አሁን ላይ ክፍት በተደረጉ እንደ ባንክ ባሉ ዘርፎች ለመሳተፍ ፍላጉት እያሳዩ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2016 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ ሀገራት ጉባኤ ጎን ለጎን ከሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የሁለትዮሽ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ እና የሕንድ መሪዎች በወቅቱ የፓርላማ ልምድ ልውውጥ ለማድረግ፣ በልማት አጋርነትን ለማጠናከር፣ በአቅም ግንበታ፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ፣ በአይሲቲ፣ በግብርና፣ የወጣቶች ክህሎት ግንባታ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግኑኝነትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች በትብብር ለመሥራት እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።

የውይይቶቹ ነጥቦችም አድገው ወደ ስምምቶች የተሸጋገሩ ሲሆን፣ ስምምነቶቹ ወደ ተግባር ተቀይረው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መጀመራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሕንድ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ 2ኛዋ ግዙፍ የውጭ ንግድ አጋር ሆነችው ሕንድ እ.አ.አ በ2021 የንግድ ልውውጣቸው 1.8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል ደርሶ ነበር።

ሕንድ ማድኃኒቶችን፣ የምግብ ዓይቶችን፣ የብረታብረት ማሸነሪዎችን፣  የፕላስቲክ ውጤቶችን፣ የወረቀት እና የጨርቃጨርቅ ምርቶችን፣ ኬሚካል፣ የትራንስፖርት ማሰሪያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ጠንካራ የንግድ አጋር ናት።

እየተገባደደ በሚገኘው የፈረንጆቹ 2025 በሕንድ እና ኢትዮጵያ መካከል ከ571 ሚሊዮን ዶላር በላይ የወጭ እና ገቢ ንግድ ልውውጥ መደረጉን መረጀዎች ያመለክታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከነጋገሯቸው የበርካታ ሀገራት መሪዎች መካከል የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ አንዱ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለሥራ ጉብኝት ዛሬ (ታኅሣሥ 07/20218 ዓ.ም) አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመሩ የትብብር መስኮችን በማስፋት ትላልቅ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ግኑኝነቶችን ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ እና ተጠቃሚነትን ለመጨመር ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።

በመሐመድ ፊጣሞ 

#EBC #EBCdotstream #Ethiopia #India #diplomaticrelations #diplomacy