Search

በአንድ ጊዜ ከ38 ሺህ በላይ ጫጩቶችን ማስፈልፈል የሚችለው የዶሮ ብዜት እና እርባታ ማዕከል

ማክሰኞ ታኅሣሥ 07, 2018 63

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ድጋፍ የተቋቋመው የጼጼ የዶሮ ብዜት እና ዕርባታ ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።

ማዕከሉ በአንድ ጊዜ ከ38 ሺህ በላይ ጫጩቶችን ማስፈልፈል የሚችል ነው።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ የጼጼ የዶሮ ብዜት እና እርባታ ማዕከል 290 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ባለፉት 6 ዓመታት 3.6 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ፥ የመደመር መንግሥት የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አንስተው፤ ይህ ሥራ በቀጣይነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የሀገራችንን የግብርና ልማት በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፥ በክልሉ የከፊል አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ኑሮ በማሻሻል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተመረቀው የጼጼ የዶሮ ብዜት እና ዕርባታ ማዕከል ጫጩት ማስፈልፈያ እና ማሳደጊያ እንዲሁም የመኖ ማቀነባበሪያን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

በነስረዲን ሀሚድ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #BenishangulGumuz #poultryfarming