"እኔ ከሻይ ጋር ያለኝ የግል ትዝታ የታወቀ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ቡናን አለመጥቀስ አይቻልም" ያሉት የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ "ቡና ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ታላቅ ገጸ በረከት ነው" ብለዋል።
"በኢትዮጵያ የቡና ሥነ ሥርዓት ላይ ሰዎች አብረው ይታደማሉ፣ ጊዜ እየነጎደ ወዳጅነት እየጠነከረ ይሄዳል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ፣ "በህንድም አንድ ኩባያ ሻይ ለመገናኘት፣ ለመጋራት እና ለመነጋገር ታላቅ ግብዣ ነው" ሲሉ ገልፀዋል።
አክለውም፣ "ልክ እንደ ኢትዮጵያ ቡና እና የህንድ ሻይ ወዳጅነታችን እየጠነከረ እና እያበበ ነው በማለት" ተናግረዋል።
ብሪክስ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን ሙሉ አባል አድርጎ መቀበሉ ታሪካዊ እርምጃ በመሆኑ እናከብራለን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ።
ህንድ ባለፉት 11 ዓመታት ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር በብዙ እጥፍ ማሳደጓን ጠቅሰው፣ በነዚህ ዓመታት ውስጥ በቀጣናዎች እና በመንግሥታት መሪዎች ደረጃ ከ100 በላይ ጉብኝቶች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ደቡቡ የዓለም ክፍል የራሱን እጣ ፈንታ እየወሰነ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ህንድ እና ኢትዮጵያም ይህን አካታች እና የራስን ዕድል የመወሰን ሂደት የሚጋሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደቡብ ደቡብ የዓለም ሥርዓት ራዕይ ሌላውን መጫን ሳይሆን ለሁሉም የሚሆን ፍትሃዊ የዓለም ሥርዓት የሚፈጠርበትን ሂደት ማመቻቸት መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
ብሪክስን የያዘው ይህ የዓለም ከፍል ፍትሃዊ የዓለም ሥርዓት፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት፣ ዓለም ብልፅግናውን የሚጋራበት እና ሉዓላዊነት የሚከበርበት የዓለም ሥርዓትን ማንበር ዋና አጀንዳው እንደሆነም ገልጸዋል።
የዓለም ሥርዓት በ1945 ከተቆለፈበት ተፈትቶ በዛሬው የዓለም እውነታ ላይ የተመሰረት እንዲሆን ካልተደረገ ዓለም ወደ ፊት መጓዝ ስለማትችል የደቡብ ደቡብ ትብብር ለዚህ መፍትሔ ለማምጣት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ህንድ ዓለም አቀፋዊ የልማት ስምምነት እንዲፈጠር አፅንዖት የሰጠችውም ለዚህ እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ፤ ቴክኖሎጂን መጋራት፣ ፍትሃዊ የፋይናንስ ሥርዓት፣ የአቅም ግንባታ፣ ዘላቂ እድገት እና ንግድ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
"ባለፈው ወር በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 ስብሰባ ላይ የአፍሪካን ክህሎት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ የሚችሉ አንድ ሚሊዮን አሰልጣኞችን ለማዘጋጀት ጥሪ ያቀረብኩትም ከዚህ እምነት ተነስቼ ነው" ብለዋል።
"ዛሬ በእህቶች እና በወንድሞች መካከል በጥልቅ የምስጋና ስሜት እና ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ በፊታችሁ ቆሜያለሁ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "መጻኢ ተስፋችን እየተጣራ ስለሆነ ተባብረን ምላሽ መስጠት አለብን" ብለዋል።
"አብረን እንጓዛለን፤ እንደ አጋር አብረን እንገነባለን፤ እንደ ወዳጅ አብረን እናሳካለን" በማለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉትን ንግግር ቋጭተዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #EBCdotstream #Ethiopia #India #parlament #DiplomaticRelations