እአአ ከ2011 ወዲህ በሕንድ መሪ ደረጃ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ የመጀመሪያው የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬድራ ሞዲ በሀገራችን ውጤታማ ቆይታ አድርገዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት እርሳቸው እንዳሉትም ከመደበኛው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተሻገረ የወንድማማችነት ግንኙነት የተጠናከረበት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ትናንት አዲስ አበባ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፤ በአየር መንገዱ ቪአይፒ ላውንጅ የኢትዮጵያን ቡና ከጋበዟቸው በኋላ ወደ ብሔራዊ ቤተመንግሥት አቅንተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕንዱ አቻቸው በብሔራዊ ቤተ መንግሥትም የክብር አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፤ ምሽቱን በተዘጋጀው የክብር እራት ላይ ደግሞ የኢትዮጵያን የክብር ኒሻን ሸልመዋቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች የሀገራቱ ልዑካን በተገኙበት ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያ እና የሕንድን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለማሳደግ የወሰኑ ሲሆን፤ ይህም ለሁለትዮሽ ትብብሩ አዲስ ጉልበት እና መነቃቃት ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የሕንድ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ እና የሕንድ-ኢትዮጵያ አጋርነት ለደቡቡ የዓለም ክፍል ያለውን ጠቀሜታ አጉልተው ገልጸዋል።
ምሽቱን በነበረው የሁለትዮሽ ውይይት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። የጉምሩክ ጉዳዮች አስተዳደራዊ ድጋፍ እና በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመረጃ ማዕከል ማቋቋምን የተመለከቱ የመግባቢያ ስምምነቶችን (MoU) ተፈራርመዋል።
በግብርና፣ በማዕድን፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት፣ በዓለም አቀፍ የሶላር ትብብር (ISA) እና በሳይበር ደኅንነት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማላቅም ተስማምተዋል።
በጤናው ዘርፍ በእናቶች እና ሕፃናት እንክብካቤ ላይ በማተኮር የማህተመ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልን ለማሻሻል እና ድጋፋቸውን ለመቀጠል ተስማምተዋል።
ሕንድ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች የምትሰጠውን የሕንድ የባህል ግንኙነት ምክር ቤት (ICCR) ስኮላርሺፕ ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ እንዲሁም በሕንድ የቴክኒክና ኢኮኖሚያዊ ትብብር (ITEC) አማካኝነት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ልዩ የአጭር ጊዜ ሥልጠና ለመጀመር ቃል ገብታለች።
በቡድን 20 የዕዳ አስተዳደር ማዕቀፍ መሠረት ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሂደት ላይ ሕንድ ለኢትዮጵያ ያላትን ድጋፍ ያሳየችበት ስምምነትም ተፈርሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የሕንድ ማኅበረሰብ አባላት ጋርም ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፤ ሕንዳውያን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈስሱ አበረታተዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBCdotstream #Ethiopia #India #AbiyAhmedAli #NarendraModi