Search

ኢትዮጵያ ከጥንት ወዳጇ ሕንድ ምን ትማራለች?

ረቡዕ ታኅሣሥ 08, 2018 64

ዘመናዊቷ ሕንድ ብዝኃነትን፣ በዓለም ላይ ትልቁን ዴሞክራሲ በማስተዳደር እና ቴክኖሎጂን በፍጥነት በማላመድ ትታወቃለች። በዚህም ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷን (GDP) 4.19 ትሪሊዮን በማድረስ የዓለማችንን 4 ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ችላለች።

በቆዳ ስፋት በዓለም ላይ 7ኛ የሆነችው ሕንድ በረጅም ታሪኳ፣ በብዝኃነቷ እና በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቷ ትለያለች። 1.43 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ በመያዝ የዓለማችን ቁጥር አንድ የሕዝብ ብዛት ያላት ሀገር ናት። ሂንዱይዝም፣ እስልምና፣ ክርስትና፣ ሲኪዝም፣ ቡድሂዝም እና ጃይኒዝም በርካታ ተከታዮች ያሏቸው ሃይማኖቶች ናቸው።

ሕንድ 705 ብሔረሰቦች በሕገ መንግሥቷ በይፋ ዕውቅና ሰጥታለች። ሒንዲ እና እንግሊዝኛ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የሥራ ቋንቋዎች ሲሆኑ፣ ሕገ መንግሥቱ 22 ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል።

ሥርዓተ መንግሥቷ ፓርላሜንታዊ ሲሆን፣ ራጃ ሳባ (የክልሎች ምክር ቤት) እና ሎክ ሳባ (የህዝብ ተወካዮች ቤት) የተባሉ ሁለት ምክር ቤቶች አሏት። ፕሬዚዳንቱ ርዕሰ ብሔር ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ርዕሰ መንግሥት ነው። በዓለም ላይ 82 ቀናትን የሚፈጅ ረጅም እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የምታካሂድ ብቸኛዋ ሀገርም ናት።

የዴሞክራሲ እናት (the mother of democracy) ተብላ የምትጠራዋ ሕንድ 28 ግዛቶች እና 8 የሕብረት ግዛቶች ውስጥ ብዝኃ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች እና ባህሎችን በማስተዳደር የዓለማችን ትልቋ ዴሞክራሲ ናት። 

ሕንድ ከድህነት ተርታ ወጥታ የዓለምን ግዙፍ ኢኮኖሚ እንድትገነባ ያስቻላት ይህ ጠንካራ ብዝኃነት እና የፌዴራል ዴሞክራሲ አስተዳደሯ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

የማንነቶች እና የቋንቋዎችን ሚዛን ጠብቆ ለብሔራዊ አንድነት ቅድሚያ በሚሰጥ፣ ነገር ግን ጠንካራ የራስ ገዝ አስተዳደርን በሚፈቅድ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ አጣምራ ሕዝቧን ታስተዳድራለች።

የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩባትም እንደ ምርጫ፣ ፍትህ እና ነጻ ፕሬስ ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት 75 ዓመታት በላይ በሀገሪቱ ፀንተው መቆየታቸው የጥንካሬዋ መሠረት ነው።

ሕንድ በዲጂታል ዘርፉ የታገዘ ጠንካራ የአስተዳደር እና የኢኮኖሚ አብዮትን ያወጀች፣ በዚህም ተጠቃሚ ሆና ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ናት። የሕንድ ዜጎችም በዲጂታል ዘርፍ በዓለም ላይ በቀዳሚነት ከሚጠሩት መካከል ናቸው።

ለሁሉም ዜጎች ማለት በሚቻል ደረጃ በዲጂታል ባዮሜትሪክ ማንነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት አሰጣጥን እውን አድርጋለች።

የተዋሃደ የክፍያዎች ሥርዓት (UPI) የተባለ የፋይናንስ አካታችነትን ሥራ ላይ በማዋል በዝቅተኛ ወጪ ዲጂታል ግብይቶችን ለማከናወን የሚያስችል ፈጣን የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጋለች።

ይህ ፈጣን የከፍያዎች ሥርዓት መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎችን በማለፍ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች አገልግሎቶችን በፍጥነት እና በብቃት እንዲሰጡ አስችሏቸዋል።

የሕንድ ኢኮኖሚ በዓለም ላይ ካሉ ኢኮኖሚዎች በጣም የተለየ እንደሆነ ይነገርለታል። በአንድ በኩል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የአይቲ እና የጠፈር ዘርፎችን የምትመራ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ድህነት፣ የመሠረተ ልማት ክፍተቶች እና ኢኮኖሚውን ያልተቀላቀለ የሰው ኃይል እንዳላት ይጠቀሳል።

ሕንድ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ለሚሆን ሕዝቧ አስፈላጊ የሆኑ እንደ የባቡር መሰረተ ልማት፣ ሜጋ ከተሞች እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የመገንባት እና የማስተዳደር ችሎታዋን በተግባር አረጋግጣለች።

በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ እና በከፍተኛ የምሕንድስና ክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለዓለም ገበያ በማቅረብ እና ከፍተኛ ገቢ በማግኘትም ትታወቃለች።

ሕንድ በባህሏ፣ ከቦሊውድ እየተመረተ ወደ ዓለም በሚሰራጨው ሲኒማዋ፣ በዮጋ እና በወሳኝ መልኩ በዳያስፖራዎቿ የዓለምን ትኩረት የያዘች እና ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላት ሀገር ናት።

ሰፊ፣ ሀብታም እና በፖለቲካ ተደማጭነት ያለው ዳያስፖራ (NRIs) ያላት ሲሆን፤ በሀገራቸው ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ ቴክኖሎጂን እንዲያመጡ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሀገራቸው የሚሟገቱ እንዲሆኑ በንቃት ታበረታታለች። በእያንዳንዱ ሥራዎቻቸው ሀገራቸውንምሳሌነት የሚያስጠሩት ልጆቿም አያሳፍሯትም።

ሕንዳውያን በየሄዱበት ባህላቸውን በጽናት በመከተል የሚታወቁ ሲሆኑ፣ ይህም የሕንድን ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ እና የንግድ ሥራ ማራኪነት አሳድጎታል።

 

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከሕንድ ምን እንማራለን?

ጥልቅ ብዝኃነት፣ ከፍተኛ የወጣት ቁጥር እና እየዘመነ ያለ ኢኮኖሚ የምትመራው ኢትዮጵያ ከሕንድ ጋር የምትጋራቸው እና የምትማራቸው በርካታ ቁምነገሮች አሉ። ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በዘርፉ ርቃ የሄደችው ሕንድ ብዙ የምታጋራቸው ልምዶች ይኖሯታል።

ኢትዮጵያ ገና ያልጎመራ ፌዴራሊዝም እና ያልተማከለ አስተዳደርን ተግባራዊ እያደረገች ያለች ሀገር ናት። በመደመር እሳቤ የብሔር ማንነትን ከሀገራዊ ማንነት ጋር ሚዛን ለማስጠበቅ እየሠራችው ላለው ሥራ የሕንድ ተሞክሮ በብዙ ይጠቅማታል።

በሥራ ላይ ያለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት አካታች እና ሚዛናዊ እንዲሆን ሕገ መንግሥታዊ እንዲሁም ተቋማዊ ሥርዓቶቿን ለማጠናከር ከሕንድ የምትማራቸው በጎ ትምህርቶች አሉ። ይህ ማለት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የባህል እና የቋንቋ መብቶችን ጠብቆ የክልሎችን እውነተኛ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማረጋገጥ ማለት ነው።

የሕንድ ምሳሌ እንደሚያሳየው የሀገርን አንድነት ለማጠናከር ጥልቅ ብዝኃነትን በማሰስ አካታች ማድረግ፣ የማያቋርጥ ድርድር እና ጠንካራ ሕገ መንግሥት እንዲሁም ነጻ እና አካታች የፍትህ ሥርዓት በጣም ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።

ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ በሚወስዱ ተቋማዊ ማሻሻያዎች ላይ ብቻ ከመተማመን ይልቅ ቴክኖሎጂን ተጠቅማ ወደ ፊት ለመዝለል እየታተረች ትገኛለች። አሁን እንደጀመረችው ለሁሉም ክፍት የሆነ እና በመንግሥት የሚደገፍ የዲጂታል ማንነት ሥርዓት እና ሁለንተናዊ የክፍያ ሥርዓት በመፍጠር ረገድ ብዙ ከተራመደችው ሕንድ  ጠቃሚ ትምህርት ይገኛል።

ዲጂታል አገልግሎት ሙስናን ለመቀነስ፣ የታክስ መሠረቱን ለማስፋት፣ ባንክ ለሌላቸው የፋይናንስ አካታችነትነት ለማፋጠን እና አገልግሎቶችን ለማሻሻል እጅግ ጠቃሚ ናቸው።

በርካታ ዳያስፖራ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ብትሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከዚህ አቅም የሚገባትን ያክል አልተጠቀመችም። ይህን አውድ ለመለወጥም ዳያስፖራዋንከሬሚታንስባሻገር የሚሄድ ተሳትፎ እንዲኖረው ሥርዓት ዘርግታ እየሠራች ትገኛለች።

ይህም የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በኢንቨስትመንት እንዲሳተፍ የባንክ እና ሌሎች ዕድሎችን መፍጠር፣ ለእውቀት ሽግግር ልዩ ማበረታቻዎችን መስጠት እና የዳያስፖራ ኔትወርኮችን ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና ለከፍተኛ ደረጃ ዲፕሎማሲ መጠቀምን ይጨምራል። ሕንድ በዚህ ረገድ የካበተ ልምዷን ልታካፍል ትችላለች።

በአጠቃላይ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች 78 ዓመታት በኋላ በጠፈር ምርምር፣ በአይሲቲ፣ በግዙፍ የጦር ኃይል እና በብቁ የሰው ኃይል የላቀ ደረጃ ላይ ከደረሰችው ሕንድ እንደ ሕዝብ እና እንደ መንግሥትም በርካታ ልምዶች ይገኛሉ። የሀገር ፍቅር፣ ባህልን መጠበቅ፣ ሌሎችን ማክበር፣ ኅብረት፣ ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት እና ጠንክሮ መሥራት ሕንዶች አርአያ የሆኑባቸው እና ልምድ የሚቀሰምባቸው ናቸው። 

በለሚ ታደሰ

#EBCdotstream #Ethiopia #India #NarendraModi