የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ እና ሕንድ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ከፍ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በጉብኝታቸው ወቅት የኢትዮጵያ ታላቅ ክብር ኒሻን ተሸልመዋል። ሁለቱም መሪዎች ባደረጓቸው ንግግሮች መፃኢው የኢትዮጵያ እና ሕንድ ጊዜ ብሩህ መሆኑን አስረግጠዋል።
ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በርካታ የአጋርነት ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
አካታች የዓለም ሥርዓታዊ ለውጥ ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን በማቅረብ የሚታወቁት የሞስኮ ነዋሪው አሜሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪው ኮሪብኮ ይህንኑ አዲሱን የኢትዮጵያ እና ሕንድ ስትራቴጂያዊ አጋርነትን በተመለከተ አምስት አስፈላጊ ነጥቦችን አቅርበዋል።
አንድሪው ኮሪብኮ እንደገለጹት አዲሱ ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑባቸው አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
1. ኢትዮጵያ እና ሕንድ የጥንታዊ ሥልጣኔዎች ባለቤቶች መሆናቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እና ሕንድ ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው የጥንታዊ ሥልጣኔዎች ባለቤቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የጥንታዊ ሥርዓተ መንግሥት እና ሥልጣኔ ባለቤቶች የሆኑት ኢትዮጵያ እና ሕንድ የዓለም ሥርዓት አካታች እና ፍትሐዊ እንዲሆን የማድረግ የካበተ ልምድ እና አቅም አላቸው።
ለዚህ የሚጠቅማቸው ደግሞ ከየትኛውም ወገን ጋር በብቸኝነት የመለጠፍ ታሪክ የሌላቸው መሆኑ ነው።
በዚህም መሠረት ሁለቱም ሀገራት የደቡብ ክፍለ ዓለም ጥምረትን ለማጠናከር እያደረጉት ያለው ጥረት ውጤት እያስገኘ ይገኛል።
2. የደቡብ ክፍል ዓለም መሪዎች መሆናቸው
አንዳንድ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የነበሩ መንግሥታት በአሁኑ ጊዜ አብዛኛውን ተፅዕኖአቸውን እያጡ መጥተዋል። ይህ ግን ለኢትዮጵያ እና ሕንድ አይሠራም።
ኢትዮጵያ እና ሕንድ አሁን ቀጣዩን የዓለም ፍትሐዊ የዓለም ሥርዓት የሚያቀናው የደቡብ ክፍለ ዓለም መሪዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ ሀገር ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ እና የቀጣናዋ አስተሳሳሪም ነች። ሕንድ ደግሞ በሕዝብ ብዛት የዓለም ቁጥር አንድ ቦታዋን የተረከበች ሲሆን፣ በደቡብ እስያ ያላት ተፅዕኖ እየጎላ የመጣ ነው።
ሁለቱም በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ የብሪክስ (BRICS) አባል ሀገራት ናቸው። በመካከላቸው የተፈጠረው ጠንካራ ትሥሥር የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ የማሻገር አቅም አለው።
የጥምረቱ አባላት ከሆኑት ከሩሲያ እና ከተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ደግሞ ብሪክስ እውነተኛ ሁሉን አካታች የዓለም ሥርዓት ለመፍጠር ለጀመረው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
3. ሰው ሠራሽ አስተውሎት በግንኙነታቸው ውስጥ ማዕከላዊ ሚና መጫወቱ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ "የሕንድ በራስ የመተማመን ራዕይ ከኢትዮጵያ የልማት ፍልስፍና ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ነው" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የመረጃ ማዕከል ለማቋቋም፣ ለተማሪዎችም ልዩ የአጭር ጊዜ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥልጠናዎችን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት በኒው ዴልሂ በሚካሄደው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስብሰባ (AI Impact Summit 2026) እንዲገኙ ተጋብዘዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ከተከታይነት ወጥታ መሪ እንድትሆን በተደጋጋሚ ከመግለጽ አልፈው በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ።
እናም በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት ከሄደችው ሕንድ የሚገኘው ድጋፍም ልምድም ከፍተኛ መሆኑ ስትራቴጂያዊ አጋርነቱ ልዩ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል።
4. ተመሳሳይ የደኅንነት ችግሮች መጋራታቸው
ኢትዮጵያ እና ሕንድ በየቀጣናቸው ከጎረቤት ሀገራት እየተነሡ ሰላማቸውን የሚያደፈርሱ አሸባሪዎች አሉባቸው። በቀጣናቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው እንዳይወጡም ለዓመታት የውልክና ጦርነት ሙከራዎች ሲደረጉባቸው የኖሩ ሀገራት ናቸው።
ይህም አሸባሪ ቡድኖችን ለመዋጋት የጋራ አቋም እንዲይዙ እና በቀጣይነት በትብብር እንዲሠሩ ያነሣሣቸዋል። ለዚህም በመካከላቸው የጠበቀ የወታደራዊ-ደኅንነት ትብብር መሥርተዋል።
5. ቀጣናዊ የባሕር ደኅንነት ፍላጎቶች
በቀይ ባሕር ቅርብ ርቀት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ከባሕሩ ተገልላ በመቆየቷ አሸባሪዎች ባሕሩ ላይ እየፈጠሩት ያለው ቀውስ ኢኮኖሚዋን እና ደኅንነቷን አደጋ ላይ እየጣለው ነው።
ሕንድ ውቅያኖስም ሌላው የባሕር ላይ ወንበዴዎች አደጋ የጋረጡበት ቀጣና ከሆነ ቆይቷል።
የእነዚህ ችግሮች እየተባባሱ መሄድ ደግሞ ኢትዮጵያ የመፍትሔው አካል ባለመደረጓ መሆኑን በርካቶች የሚያነሡት ጉዳይ ነው።
ይህም ሁለቱም ሀገራት የጋራ የደኅንነት ችግራቸው በሆነው የባሕር ላይ ጥምረታቸውን እንዲያጠናክሩ ያደርጋቸዋል።
ሕንድ፣ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የባሕር በሯን እንድታገኝ ድጋፏን የሰጠች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር በማጥበቅ ጥቅሟን ማስጠበቅ ትፈልጋለች።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #India #diplomacy #HornofAfrica