Search

በባህር ዳር ከተማ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ተጨባጭ ለውጦች ታይተዋል - የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል

ዓርብ ታኅሣሥ 10, 2018 48

የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ልዑክ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ መስኮች የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝቷል።
ካውንስሉ በኢንዱስትሪዎች የሚፈጠሩ ማነቆዎችን ለመፍታት የተሰማራ ኮሚቴ መሆኑን የገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ እና የካውንስሉ ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከአምራቾች ጋር በመቀራረብና ፋብሪካዎችን በመመልከት ችግሮች እንዲፈቱ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍ እንዲል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም በዘርፉ እየታዩ ያሉ ለውጦች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እያደገ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በዛሬው ዕለትም የብረታ ብረት፣ የምግብ ዘይት፣ የእንስሳት መኖ ፋብሪካና በሌሎችም ምርቶች የተሰማሩ አምራቾችን መመልከታቸውን የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየቱን ገልጸዋል። የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በጥሩ ሁኔታ እያደገ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ በባህር ዳር ከተማ በተደረገው ጉብኝት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ዕድገት እያሳየ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ባህር ዳር ከተማን ጨምሮ በክልሉ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተዋል።
የወጪ ንግድ እና ተኪ ምርቶችን በስፋት ከማምረት አንጻርም ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየቱን ተናግረዋል።
ከለውጡ ወዲህ በዘርፉ የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ምቹ ሁኔታ በመፍጠራቸው ተጨባጭ ለውጦች ታይተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የተለያዩ የመሠረተ ልማት እና መሰል ችግሮች እንዲሟሉ በአምራቾች ዘንድ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፤ ካውንስሉ የተነሱ ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት እንደሚሠራ ተገልጿል።
በጉብኝቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፣ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
 
በሳሙኤል ወርቅዓየሁ