የሶማሊ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የሴክተሮች ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አክሊሉ ታደሰ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
በ9 ተቋማቶች 32 አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር የሚሰጠው ሶማሊ መሶብ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል።
በምረቃው ወቅት የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ፤ ማዕከሉ የሰውን ክብር የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል ዘመናዊ መሰረተ ልማት እና የሰው ሀይል መሟላቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ 13 ከተሞች ላይ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ነው የገለፁት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የሴክተሮች ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አክሊሉ ታደሰ፤ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመንግስት አገልግሎት ዘርፉ ይስተዋል የነበረውን ዝለት በማስቀረት ሰው ተኮር የአገልግሎት ልህቀትን የማረጋገጥና ዜጎችን የማክበር ማሳያ ነው ብለዋል።
በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር በማካተት፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያግዛልም ሲሉ ተናግረዋል።
ማዕከሉ አገልግሎት ፈላጊ ዜጎች በፍትሀዊነት እና በውጤታማነት የሚስተናገዱበትን ስርዓት ለመዝረጋት የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑም ተጠቁሟል።
በቴዎድሮስ ታደሰ
#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #Somali #MesobCenter