ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ጋር በመተባበር አሉታዊ መጤ ባህሎች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና የማህበረሰቡን ተጠቂነት ለመቀነስ ያለመ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመህዲ፥ ኢትዮጵያ የሚያስተሳስሩ እና አንድነትን የሚያጠናክሩ በርካታ የባህል እሴቶች ባለቤት ናት ብለዋል።
በዘመናዊነት ስም የምንከተላቸው አሉታዊ መጤ ባህሎች እና ልማዶች ለማህበራዊ መስተጋብር መሠረት የሆኑ እሴቶች እንዲሸረሸሩ፣ የእምነት ሥርዓቶች እንዳይከበሩ፣ በማንነቱ የማይኮራ ትውልድ እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆኑ አብራርተዋል።

መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ይህን ለመከላከል የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች እና አደረጃጀቶችን በመፍጠር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከዘመን አመጣሽ አሉታዊ መጤ ባህሎች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ራስን በመጠበቅ፣ ጠቃሚ ባህላዊ እሴቶችን በማጎልበት ብቁ እና ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የየድርሻውን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ወጣቶችም የተዛባ አለባበስን መከተል እና አደንዛዥ ዕፅ መጠቀምን ጨምሮ ከኢትዮጵያውያን ባህል እና እሴት ላፈነገጡ ተግባራት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ራሳቸውን እንዲጠብቁና ሌሎችንም እንዲከላከሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ በችግሩ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመሐሪ ዓለሙ