Search

አርባ ምንጭና አባያ ሐይቅን - ለላቀ የቱሪዝም መዳረሻነት

ረቡዕ ታኅሣሥ 15, 2018 137

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምትገኘው አርባምንጭ ከተማ የበርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት ናት። አርባዎቹ ምንጮችና በውስጣቸው ያሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የአርባ ምንጭ ደን፣ የመደመር ተንጠልጣይ ድልድይ፣ የአባያና ጫሞ ሐይቆች፣ አዞ ራንች እንዲሁም ሁለቱን ሐይቆች የሚያገናኘው የእግዜር ድልድይ በዋነኝነት የሚጠቀሱ መስህቦች ናቸው።
 
በክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተመራ የሚዲያ ባለሙያዎች ልዑክ በአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን ጎብኝቷል።
የአርባምንጭ ከተማ የቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ ደምበላ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ በከተማዋ የሚገኙ የመስህብ ሥፍራዎችን ይበልጥ በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
በሐይቁ ላይ የጀልባ ትራንስፖርት አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ የጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩን አንስተው፤ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
 
ከቱሪዝም ልማቱ ጎን ለጎን በሐይቁ ዙሪያ እየተዛመተ የሚገኘውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የተጠናከረ ሥራ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በአባያ ሐይቅ ላይ የተጀመረውን የጀልባ ትራንስፖርት አገልግሎት በማስፋፋት ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
 
በተመስገን ተስፋዬ