የቱሪዝም ዘርፍ ከሀገራዊ የልማት አጀንዳ ውስጥ አንዱ የስትራቴጂክ ምሰሶ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።
መንግሥት የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል፣ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እና የአገሪቱን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱንና በዚህም አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አገልግሎቱ አስታውቋል።
አገልግሎቱ እንዳመለከተው፣ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሃገር እና ገበታ ለትውልድ የተሠሩት የወንጪ ደንዲ፣ ጎርጎራና ሀላላ ኬላ ኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክቶች እንዲሁም በብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ኢኮ-ሎጆች የአካባቢ፣ የባህል ጥበቃን እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ያጣመረ አዲስ የዘርፉ እሳቤ መሆኑን ያሳያሉ ብሏል።
ይህም በተፈጥሮ ማራኪ የሆኑ ስፍራዎችን ወደ ሀብትነት በመቀየርና የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን በመሳብ ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ እንዲነቃቃ ማድረግ መቻሉን ገልጿል።
የቱሪዝም ዘርፍ የሀገሪቱን የበለጸጉ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጠቀም፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዋና ምንጭ እና ሁሉን አቀፍ እድገት አንቀሳቃሽ እየሆነ መምጣቱን አገልግሎቱ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ ያላትን ቅርሶች በማደስ፣ በመጠበቅ፣ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡና ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ መሠራቱንም አገልግሎቱ እንዳመለከተው ለመረዳት ተችሏል ብሏል።
ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት የኢትዮጵያን ገጽታ ከማስተዋወቅና ቱሪዝምን ከማነቃቃት ባሻገር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እያጠናከሩ መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴም ለጋራ ትርክት ግንባታና ብሔራዊ ገጽታን ለማስረጽ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቁሟል።
በሌላ በኩል አዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻ፣ የኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ሥራ መሠራቱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።
የከተማ ማስዋቢያ ፕሮጀክቶችንና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ የእንግዳ ተቀባይነትን በማሻሻል እና የባህልና ኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማስተዋወቅ አዲስ አበባን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በልዩ ትኩረት በተሠራ ሥራ፤ ከተማዋ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ ተመራጭ እየሆነች መምጣቷን አገልግሎቱ አስታውቋል።
አሁን ላይ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችን ማልማትና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማደስ መሆኑንና በዚህም ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውን አገልግሎቱ ገልጿል። እነዚህ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን እና ሁሉን አቀፍ ልማትን ለመደገፍ የታለሙ መሆናቸውንም አመልክቷል።
መንግሥት በዘርፉ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉ ሌላኛው ወሳኝ ስኬት መሆኑን የገለጸው አገልግሎቱ፤ ይህም የተቋማዊ ቅንጅት እንዲጠናከር ከማድረጉም ባሻገር ቱሪዝምን ከመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ ዲጂታል ሽግግር እና የሥራ ፈጠራን ጨምሮ ጠንካራ የሆነ ሀገራዊ ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ ማስቻሉን አስታውቋል። ይህም በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን አገልግሎቱ ገልጿል።
በአጠቃላይ የሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ራዕይ አካታችነትን ማሳደግ፣ የአካባቢ ማኅበረሰቦችን በማሳተፍ፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማበረታታት እና የኢኮኖሚ እድገቱን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
#ebcdotstream #EBC #tourism