በአዲስ አበባ አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን እንዲቀንሱ የሚያነቁ የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎች እየተሰሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በከተማዋ በአይነቱ ለየት ያለ አሽከርካሪዎችን የሚያነቁ የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎች የቀለም ቅብ እየተከናወነ መሆኑን በባለስልጣኑ የመንገድ ደህንነት ምህንድስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር መርጋ ሰፈራ ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ተናግረዋል፡፡
የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎቹ ንዝረትን በመፍጠር አሽከርካሪዎች ፍጥነት እንዲቀንሱ በማድረግ የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
አሽከርካሪዎች እንደየመንገዱ የፍጥነት ወሰን እንዲያሽከረክሩ፣ ከፊት ለፊታቸው ያለውን የመንገድ ሁኔታ እንዲያውቁ፣ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲያሽከረክሩ እንዲሁም ለእግረኞች ቅድሚያ እንዲሰጡ እንደሚረዳ ነው የጠቀሱት፡፡
ማንቂያዎቹ በፍጥነት ምክንያት በተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ ይደርስባቸዋል ተብለው በጥናት በተለዩ ቁልቁለታማ ቦታዎች፣ መጋጠሚያ አካባቢዎች፣ ወደ አደባባይ መግቢያ ሥፍራዎች እና የትራፊክ መብራት በሌለባቸው መስመሮች ላይ እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ፒያሳ፣ ከሚክሲኮ ወደ ሳርቤት፣ ሀጫሉ መንገድ፣ ከለቡ መብራት እስከ ለቡ መድኃኒዓለም፣ ዓድዋ ሙዚዬም፣ ቤተ መንግሥት አካባቢ፣ ከካዛንቺስ - ሴቶች አደባባይ፣ ከካዛንቺስ ወደ ቤተመንግሥት፣ ከቤተ-መንግሥት- ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ከአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ወደ ቀይ ባሕር ኮንዶሚኒየም እንዲሁም በወንዝ ዳር ፕሮጅክቶች ያሉ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች ማንቂያዎቹ ከተሰሩባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በቀጣይም በትምህርት ቤቶች፣ በኃይማኖት ተቋማት፣ በገበያ ማዕከላት እና እግረኛ በሚበዛባቸው ሥፍራዎች አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን እንዲቀንሱ የሚያነቁ የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
በየተመኙሽ አያሌው