ከአንድ ሀገር የዕድገት መለኪያዎች መካከል የመንገድ መሠረተ ልማት ደረጃ ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙት የልማት ሥራዎች መካከል አንዱ ነው። የመንገድ መሠረተ ልማት በሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ላይ እመርታ እንዲታይ የሚረዳ ሲሆን፤ የከተማና የገጠር ትስስርንም ማጠናከር ያስችላል።
ዘመኑን የሚመጥኑና ደረጃውን የጠበቁ ዘመናዊ የፍጥነት መንገድ መሠረተ ልማቶች ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚጫወቱት ሚና የላቀ ነው። ጥራቱን የጠበቀ ፈጣን መንገድ የጊዜና የነዳጅ ብክነትን በመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ጫናን በተወሰነ ደረጃ ያቃልላሉ፤ የሥራ ቅልጥፍናን ይጨምራሉ።
የተሽከርካሪዎችን ጫና በማቃለል የአገልግሎት ቆይታቸው የተሻለ እንዲሆንና ለመለዋወጫዎች የሚወጣውን ወጪ በመቀነስ ረገድም ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።
በቆይታ ምክንያት የሚበላሹ ምርቶች (Perishable goods) በሚፈለገው ሰዓት ወደ መዳረሻቸው እንዲጓጓዙ ፈጣን መንገዶች ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው። የመደመር መንግሥት ለመንገድ መሠረተ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን፤ ፈጣን መንገዶችም ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታቸው ታምኖባቸው በከፍተኛ ትኩረት እየተገነቡም ነው።
የፈጣን መንገድ ፕሮጀክቶች በራሳቸው ገቢ የሚያስገኙ፣ የጥገና ወጪያቸውን መሸፈን የሚችሉና በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ሌላው ጠቀሜታቸው ነው።

በግንባታ ላይ ያሉና ሊገነቡ የታሰቡት የፍጥነት መንገዶች ምን ያህል ናቸው?
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፍጥነት መንገድ የአዲስ አበባ - አዳማ የፍጥነት መንገድ ነው። ይህ መንገድ ከምሥራቅና ከመካከለኛው አፍሪካም ቀዳሚው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው። ከአዲስ አበባ - አዳማ የፍጥነት መንገድ ቀጥሎ የተገነቡት የድሬዳዋ - ደወሌ እና የሞጆ - ባቱ የፍጥነት መንገዶች ሲሆኑ፤ እነዚህ ሲደመሩ 391 ኪ.ሜ ይሸፍናሉ።
መንገዶቹ ከዚህ ቀደም ይከሰት የነበረውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በማስቀረት፣ የወጪና ገቢ ንግዱ የተሳለጠና ቀልጣፋ እንዲሆን ትልቁን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ።
በግንባታ ላይ ያሉ የፍጥነት መንገዶች
57 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቱ - አርሲ ነገሌ - ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ 96 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በቅርቡ ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል።

ሌላኛው በግንባታ ላይ ያለ የፍጥነት መንገድ 52 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው አርሲ ነገሌ - ሐዋሳ የፍጥነትና ክፍያ መንገድ ሲሆን፤ ሥራው 64.5 በመቶ ተጠናቅቋል።
ግንባታው 46 በመቶ የደረሰው የአዳማ - አዋሽ ሎት 1 የፍጥነትና ክፍያ መንገድ ደግሞ 61.5 በመቶ ሥራው ተከናውኗል፤ ግንባታውም በፍጥነት እየሄደ መሆኑ ተጠቁሟል።
የመኤሶ - ድሬዳዋ የፍጥነትና ክፍያ መንገድ በቅርቡ ግንባታው የተጀመረ ሲሆን፤ ርዝመቱ 144 ኪሎ ሜትር እንደሆነ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመላክታል። የእነዚህ አዳዲስ የፍጥነት መንገዶች አጠቃላይ ርዝመት 314.5 ኪሎ ሜትር ነው።
67 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው አዳማ - አዋሽ ሎት 2 የፍጥነትና ክፍያ መንገድ በጨረታ ሒደት ላይ ሲሆን፤ በፋይናንሰር ለመጽደቅ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሶ የቅድመ ጨረታ ሒደቱ ተጀምሯል። 65 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን የመኢሶ - ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድን ለማስጀመር ከልማት አጋሮች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

ከአዲስ አበባ በዋና ዋና መውጫ በሮች በኩል የፍጥነት መንገዶችን መገንባትም መንግሥት በዕቅድ የያዘው ጉዳይ ነው። በዚህም መሠረት አዲስ አበባ - ጅማ፣ አዲስ አበባ - ነቀምት፣ አዲስ አበባ - ደብረ ማርቆስ እና አዲስ አበባ - ኮምቦልቻ በሚሄዱ መንገዶች ላይ የአዋጪነት ጥናት እየተካሄደ መሆኑም ነው የተገለጸው።
እነዚህ መንገዶች ከፍተኛ ወጪ የሚወጣባቸው በመሆኑ፣ ተጠናቅቀው አገልግሎት ሲጀምሩ የአገልግሎት ዕድሜያቸውና ጥራታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
ቁጥጥሩም ከሥራ ተቋራጭና አማካሪ መሐንዲስ የጥራት መፈተሻ የተሟላ ላቦራቶሪ ከማደራጀት ጀምሮ፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከሀገር ውጭ የላቦራቶሪ ፍተሻ እስከማድረግ ድረስ የሚዘልቅ መሆኑ ን ነው ባለስልጣኑ ያመላከተው።
መንገዶቹ ከመደበኛ መንገድ ፍሰት የተለዩ በመሆናቸው ጥራታቸው ላይ ምንም ዓይነት ድርድር እንደማይኖር መንግሥት አቋም ይዞ እየሠራ ይገኛል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #EBCDotstream #road #expressroad #infrastructure