በባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የአፈር ለምነትን በመጨመር ለግብርና ምርት እድገት እገዛ ማድረጋቸውን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።
በሲዳማ ክልል የ2018 የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በሰሜን ሲዳማ ዞን በሐዌላ ወረዳ ቅሾ ተፋሰስ ተጀምሯል።
በተደራጀ የሕዝብ ተሳትፎ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ለአንድ ወር የሚቆይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የሚከናወን ይሆናል።
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ለግብርና ምርት እድገት እገዛ ማድረጉን ገልጸው፤ የክልሉ ነዋሪ ለዚህ ሥራ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በዘመቻው 147 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የማህበረስብ ክፍሎችን በማሳተፍ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
በተለይ በክልሉ የባሕርዛፍ ተክል በአፈር ለምነት ላይ የሚያሳድረውን ጉዳት ለመከላከል ከእርሻ መሬቶች ላይ የማንሳት ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዚህም ከዘመቻ ሥራው ጋር በተቀናጀ መንገድ ከ 8 ሺህ 500 ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ የባሕርዛፍ ተክልን ለመንሳት ታቅዷል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 22 ሺህ ሄክታር መሬትን ከባሕርዛፍ ተክል ነፃ በማድረግ ለእርሻ ሥራ እንዲውል ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።
በሚካኤል ገዙ