Search

የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቶች

ዓርብ ጥር 15, 2018 340

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሳሽነት 2011 . በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስከ አሁን 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

ይህ መርሐ ግብር በአሁኑ ወቅት ከችግኝ ተከላ አልፎ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ትሩፋቶችን እያስገኘ ነው።

የኢትዮጵያን የተራቆቱ መሬቶች መልሶ በማልማት ረገድ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ባለፉት ሰባት ዓመታት በተሠራው ተከታታይ ሥራ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 2011 . ከነበረበት 17.2 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ብሏል።

የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎች በአረንጓዴ ተክሎች በመሸፈናቸው የአፈር መሸርሸር ቀንሷል፤ የከርሰ ምድር ውኃ መጠን እንዲጨምር እና የደረቁ ምንጮች እንደገና እንዲፈልቁ አድርጓል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩት ችግኞች ካርቦን በመምጠጥ የአየር ብክለትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙ ሲሆን፣ የዝናብ ወቅትም እየተስተካከለ መሆኑ በተግባር እየታየ ያለ ጉዳይ ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ አካባቢ እንዲያገግም እና የአየር ንብረት እንዲስተካከል ከማድረግም አልፎ የምግብ ዋስትና እና የኢኮኖሚ (Food Security & Economy) ፋይዳው ከፍ እያለ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ ከጥላ እና ጫካ ዛፎች ጎን ለጎን ለምግብነት የሚውሉ (Edible) ችግኞች ላይ ትኩረት ተደርጎ በመሠራቱ የመርሐ ግብሩ ትሩፋቶች የሆኑት የፍራፍሬ ዛፎች የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ጀምረዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ እና አፕል ችግኞች በመተከላቸው አርሶ አደሮች እና የከተማ ነዋሪዎች የምግብ ፍጆታቸውን እንዲያሟሉ እና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ በተተከሉት ችግኞች የአቮካዶ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ ኢትዮጵያ ወደተለያዩ ሀገራት ፍራፍሬ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ጀምራለች።

በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የምግብ ሥርዓት ከመገንባት ባለፈም ለብዝኃ ሕይወት መጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።

መርሐ ግብሩ በየዓመቱ ለበርካታ ዜጎች፣ በተለይም ለሴቶች እና ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ፈጥሯል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋሙት 120 ሺህ በላይ የችግኝ ጣቢያዎች በችግኝ ማፍላት፣ ተከላ እና እንክብካቤ ሥራ ላይ በርካታ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል አግኝተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋት በከተሞችም በጉልህ ይታያል። እንደ ገበታ ለሸገር እና የኮሪደር ልማት ያሉ ፕሮጀክቶች የዚህ ጠቀሜታ ማሳያዎች ናቸው።

በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልል ከተሞች የተገነቡት ፓርኮች የከተማ ነዋሪዎች ንጹህ አየር የሚያገኙባቸው እና የሚዝናኑባቸው ቦታዎች ሆነዋል። ከፍተኛ ሙቀት በመቀነስ ከተሞች ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ እያደረጉ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ልምዷን ለጎረቤት ሀገራትም በማካፈል ቀጣናዊ ትስስርን እያጠናከረችበት ነው። ጅቡቲ፣ ደቡብ እና ኬንያ በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ። ይህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ለውጥ ያላትን ቁርጠኝነት ለዚህም የወሰደችውም የአመራርነት ሚናዋን አሳይቷል።

ትልቁ እና ዘላቂ ትሩፋቱ ደግሞ ሕዝቡ በተለይም ሕፃናት እና ወጣቶች ዛፍ የመትከል እና የመንከባከብ ባህልን እንዲያዳብሩ ማስቻሉ ነው።

ዛፍን መትከል እንደ አንድ ብሔራዊ ግዴታ እና ባህል ተቆጥሮ "የነገን ዛሬ መትከል" የሚለው አስተሳሰብ በሕዝቡ ዘንድ ሰርጿል።

አረንጓዴ ዐሻራ በዛፍ ቁጥር ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ (Green Economy) በመለወጥ ረገድ ያስቀመጠው ጽኑ መሠረት ነው።

በለሚ ታደሰ