Search

የ6 ወር እቅድ አፈፃፀማችንን በአማካይ 95.3 በመቶ ማሳካት ችለናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዓርብ ጥር 29, 2018 52

3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም አቅርበዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት የ 6 ወር እቅድ አፈፃፀማችንን በአማካይ 95.3 በመቶ ማሳካት ችለናል ብለዋል።
 
የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በተሰራው ሥራ 23 አዳዲስ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ የተደረገ ሲሆን ፣ አሁን ላይም በአጠቃላይ 370 አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲሰጡ ማድረግ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
የኤሌክትሮኒክ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓትን ሁሉም ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በ67 ጤና ተቋማት የጤና መረጃ ስርዓቱን ሙሉ ለሙሉ ወረቀት አልባ ማድረግ ተችሏል፤ ይህም ከእቅዱ 117 በመቶ በላይ ነው ብለዋል።
በቅድመ አንደኛና አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ 940 ሺ 329 በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ እየተደረገ ሲሆን፣ የተማሪ ዩኒፎርም፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና የመምህራን ጋዋን በወቅቱ እንዲደርሳቸው መደረጉን አንስተዋል።
ይህም በኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች (መጠነ ማቋረጥ)፤የሚደግሙ (ተማሪዎች መጠነ መድገም) ጉልህ በሆነ መልኩ መቀነስ እንዲሁም በተማሪዎች መካከል የእኩልነት ስሜት በማዳበር የስነ-ልቦና ጫናን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡
የሰላም ሠራዊት ተሳትፎ ከማሳደግ አኳያ ከ22 ሺህ በላይ አዳዲስ የሰላም ሠራዊት አባላትን በመመልመልና በማሰልጠን ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት በየቀኑ ለከተማዋ ሰላም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መደረጉንም ገልጸዋል።
የንግድ ሕጋዊነትን በማስፈን ረገድ በ230 ሺ 13 ድርጅቶች ላይ ክትትል ተደርጎ፣ 12 ሺ 139 ጥፋተኞች መለየታቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 10 ሺ 496 ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ መስመር መመለሳቸውን አስታውቀዋል።
7 ሺ 400 መደበኛ ላልሆኑ አነስተኛ ንግዶችን ሕጋዊ እውቅና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።