በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት ሥርዓት በቴክኖሎጂ ታግዞ ገጽታውን እየቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባልነቷን ተጠቅማ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች። ይህ ጉዞ የላቀ ቴክኖሎጂን ከሰው ተኮር ማኅበራዊ ድጋፎች ጋር በማቀናጀት ለደቡባዊው የዓለም ክፍል (Global South) አዲስ ተስፋ እየፈነጠቀ ነው።
የብሪክስ ትብብር እና የዲጂታል ትምህርት ፋይዳ
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ካሉ የትምህርት ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ሕፃናት መካከል ሲሶ የሚበልጡት (35.9 በመቶ) የሚኖሩት በብሪክስ አባል ሀገራት ውስጥ መሆኑ፣ ስብስቡ በዓለም አቀፍ የትምህርት አጀንዳ ላይ ያለውን ወሳኝ ድርሻ ያሳያል።
ኢትዮጵያም የዚህ ግዙፍ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕቀፍ ተጠቃሚ ለመሆን የኦንላይን ትምህርትንና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አጠቃቀምን እንደ ዋነኛ መፍትሔ ይዛ ተነሥታለች። በአውሮፓውያኑ እስከ 2030 ድረስ በጋራ የትምህርት ፕሮግራሞች የሚሳተፉ ተማሪዎች ቁጥር 100 ሺህ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም ለኢትዮጵያ ወጣቶች የዓለም አቀፍ የልምድ ልውውጥ በር ይከፍታል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ማዕከል የመሆን ጉዞ
ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ የሰጠችውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ እየተመዘገበ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓይነቱ ሁለተኛ የሆነውን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት የተደረገው ዝግጅት፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ የታለመ ነው። ይህ ተቋም በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል ለሚከናወነው የሳይንስ ጥምረት እንደ ዋነኛ ድልድይ የሚያገለግል ሲሆን፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የሀገራዊ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን ያፋጥነዋል።
ማኅበራዊ ድጋፍ እንደ ትምህርት ስኬት መሠረት
የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ግስጋሴው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ እንደ ብራዚልና ሕንድ ያሉ የብሪክስ አባል ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም አስደናቂ ውጤት እያመዘገበች ነው። የትምህርት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአሁኑ ወቅት ከ9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በአዲስ አበባ ብቻ በቀን ሁለት ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች መኖራቸው፣ ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የተከፈለ ትልቅ ዋጋ ነው።
ይህ ተግባር ትምህርታዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እመርታንም አስመዝግቧል። የምገባ ፕሮግራሙን ተከተሎ የተማሪዎች የትምህርት ማቋረጥ መጠን በአማካይ ከ15 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጎታል። በሌላ በኩል፣ ፕሮግራሙን ለማስፈጸም ከ25 ሺህ በላይ እናቶች በምግብ ዝግጅትና በሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው፣ በትምህርት ዘርፍ የሚደረግ ኢንቨስትመንት እንዴት ማኅበረሰብን እንደሚቀይር ማሳያ ነው።
የወደፊት እይታ፦ የፖሊሲ ትኩረትና ተግዳሮቶች
ምንም እንኳን የዲጂታል ክፍተት እና የፋይናንስ እጥረት አሁንም ፈታኝ ሆነው ቢቀጥሉም፣ የኢትዮጵያ አቅጣጫ ትምህርትን የሰው ኃይልና የኢኮኖሚ ልማት ሞተር ለማድረግ የተቃኘ ነው። በአንድ በኩል ዘመናዊውን የ-AI ዩኒቨርሲቲን በመገንባት የወደፊቱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማረጋገጥ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎችን ጤናና ተሳትፎ መጠበቅ፣ ኢትዮጵያ በዲጂታላይዜሽንና በተጠቃሚነት ዘርፍ የጀመረችው ሽግግር ስኬታማ መሆኑን ያረጋግጣል።
ይህ ሚዛናዊ ጉዞ ለደቡባዊው የዓለም ክፍል ሀገራት በትልቅ አርአያነት የሚጠቀስና ትምህርትን በሁለንተናዊ መልኩ ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው።
በሰለሞን ገዳ