Search

የጋሼና - ላሊበላ - ሰቆጣ መንገድ ፕሮጀክት የአስፋልት ንጣፍ ሥራ ተጀመረ

ረቡዕ መጋቢት 09, 2018 15

በአማራ ክልል የሰሜን ወሎን ከዋግኽምራ ዞን ጋር የሚያስተሳስረው የጋሼና - ላሊበላ - ሰቆጣ መንገድ ፕሮጀክት የአስፋልት ንጣፍ ሥራ ተጀምሯል።
በሁለት ኮንትራክተሮች ተከፋፍሎ የሚገነባው ይህ ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክት የጋሼና - ብልባላ፣ የላሊበላ ከተማ ተለዋጭ መንገድ እና የብልባላ - ሰቆጣ መስመሮችን ያካትታል።
ለግንባታው በፌደራል መንግሥት 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበለት ሲሆን፣ ሥራውን ኅብር ኮንስትራክሽን ከዘመን ኮንስትራክሽን ጋር በጣምራ እያከናወኑት ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት በሰቆጣ፣ ላሊበላ እና ጋሼና ከተሞች የአስፋልት ንጣፍ፣ የአፈር ቆረጣና የሲሚንቶ ኮንክሪት ሥራዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ነው።
ተቋርጦ የነበረው ይህ ፕሮጀክት እንደገና በመጀመሩ የአካባቢውን ማኅበራዊና ምጣኔ-ሃብታዊ መስተጋብር ከማሳደጉ ባለፈ፣ የላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናትን ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያነቃቃ ይጠበቃል።
መንገዱ ሲጠናቀቅ የዋድላ፣ መቄት፣ ላስታና ጋዝጊብላ ወረዳዎችን በማገናኘት የትራንስፖርት ፍሰቱን በእጅጉ ያቀላጥፋል።