Search

በመዲናዋ የመረዳዳት እና የመተሳሰብ ባህል እየዳበረ ነው፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዓርብ መጋቢት 11, 2018 43

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ1447ኛውን የዒድ አል-ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ በመዲናዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 28ቱም "የተስፋ ብርሃን" የምገባ ማዕከላት አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንን እና ለከፋ ማህበራዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ማዕድ የማቋደስ መርሃ ግብር አከናውነዋል።
ከንቲባዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ በሚገኘው 6ኛው እና በኮልፌ ቀራኒዮ በሚገኘው 21ኛው የምገባ ማዕከላት በአካል በመገኘት ማዕድ ያጋሩ ሲሆን፣ ማዕከላቱ በዓቢይ ጾም እና በረመዳን ወቅትም ለጾመኞች እንደየ እምነታቸው የአፍጥር እና የጾም ምገባ አገልግሎት ሰጥተዋል።
ከንቲባዋ በማዕድ ማጋራት መርሐ ግብሩ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ የመረዳዳት እንዲሁም የመተሳሰብ ባህል በከፍተኛ ሁኔታ እየዳበረ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተከናወነው የበጎ አድራጎት ተግባር፣ ነዋሪው እርስ በእርሱ የሚተጋገዝበትን እና አንድነቱን የሚያጠናክርበትን መልካም እሴት በተግባር የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጥሪውን ተቀብለው በማዕከላቱ ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ ባለሀብቶች፣ አጋሮች እና አስተባባሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበው በዓሉ የደስታና አብሮነት የሚጎለብትበት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
በወንደሰን አፈወርቅ