Search

ለጋሞ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎች የተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል

ዓርብ መጋቢት 11, 2018 46

በጋሞ ዞን ደጋማ አካባቢዎች በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለት የመከላከያ ሚኒስቴር የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ በራሱ ማሳ ያመረተውን 100 ኩንታል በቆሎ ለዞኑ አስተዳደር ያስረከበ ሲሆን፣ የዕዙ የሠራዊት ሥነ-ልቦና ግንባታ ኃላፊ ኮሎኔል ሌቺሳ መገርሳ ድጋፉ የሠራዊቱን አለኝታነት ለማሳየት ከጅማ እና አርባ ምንጭ ድጋፍ ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የፌደራል መንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን 5 መቶ ሺህ ብር የሚያወጣ የእህል ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሠረት መስቀሌ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ከጎፋ ዞን አስተዳደር 12 መዋቅሮች የተወጣጡ የመንግሥት ተቋማትም ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የጥሬ ገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ያበረከቱ ሲሆን፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በተለይ የመከላከያ ሠራዊት የሀገር ዳር ድንበር ከመጠበቅ ባለፈ በተፈጥሮ አደጋ ወቅት ለህዝብ ያለውን ተቆርቋሪነት በተግባር እያሳየ መሆኑን አድንቀዋል።
ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ደጋግ ኢትዮጵያውያን እና የሀገር ወዳጆች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል።
በተመስገን ተስፋዬ