ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ መጪውን የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ፤ ለማኅበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ጧሪ እና ደጋፊ ለሌላቸው የአገር ባለውለታ አረጋውያንና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች በአጠቃላይ ከ233 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ማዕድ ማጋራታቸውን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ ይህ ተግባር በከተማዋ የማዕከል መስሪያ ቤቶች፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች እየተከናወነ ያለ በጎ ተግባር ነው።
“በሁሉም በዓላት የምናደርገው የማዕድ ማጋራት፤ ድጋፍ የሚሹ የከተማችን ነዋሪዎችን “ምን ጎደለ?" ብለን በመመልከትና በመጠየቅ ክፍተታቸውን የምንሞላበት ለነዋሪዎቻችን ያለንን ክብር የገለፅንበት ሰው ተኮር ተግባር ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
ማዕድ ከማጋራት ባለፈ አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ግጭት እና በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የሚከሰተውን ጊዜያዊ የኑሮ ጫና ለማቃለልና የገበያ ጉድለትን ለመሙላት፣ ከፍተኛ በጀት መድበን መሰረታዊ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
በዚህም የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በተሠራው ሥራ፣ በከተማዋ የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ እንዲሰፍን መደረጉን ተናግረዋል።
ወቅታዊ ችግሮችን ለመሻገር የምናከናውናቸው እነዚህ ተግባራት በሙሉ ከለውጡ ወዲህ የጀመርነው የ"ሰው ተኮር" ሥራዎቻችን አካል ናቸው ነው ያሉት።
“አዲስ አበባ ለሀብታሙም ለድሃውም፣ ለሁሉም እኩል የተመቸች፣ ስራዎቻችንም ማንንም ያልዘነጉ አካታች እንዲሆኑ እየሰራን ሲሆን፤ ከተማዋ እየተቀየረችና እየተለወጠችበት ያለው ልማት በሰዉ ኑሮና አኗኗር ላይ ለውጥ እያመጣ ያለ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
"መስጠት አያጎድልም" ብለን ባደረግንላቸው ጥሪ መሰረት በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለሚደረገው ማዕድ ማጋራት ለተባበሩ ልበ ቀና ባለሀብቶች፣ እንዲሁም ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻቸው ሁሌም እየተሸከሙ በጉልበታቸው በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ላሉ ወጣቶች በሙሉ በራሳቸው እና በነዋሪች ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይም ዛሬ በከንቲባ ፅ/ቤት ያካፈልነውን ያቀረቡልን Jospong integrated waste management plc 15 ሚሊዮን ብር፣. አቶ ጀማል (ሚድሮክ) 10 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን 7 ሚሊዮን ብር፣ አቶ በላይነህ ክንዴ (BKG) 5 ሚሊዮን ብር፣. አትሌት ዮሐንስ ቢፋ 2.9 ሚሊዮን ብር፣ አቶ ተካበ ሙሉ 500 ሺህ ብር በመለገሳቸው ከልብ አመስግነዋል።