የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በ2025ቱ የአፍሪካ ፓለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ብልጽግና ፓርቲ በ'መደመር' እሳቤ የተወለደ ሕዝባዊ ፓርቲ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ'መደመር' መርሕ በአንድነት፣ በጋራ አስተዋፅኦ እና በጋራ ዓላማ የተገነባውን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዟችንን ይወክላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ አካታች የፖለቲካ ሥርዓት በመዘርጋት ብልጽግና ፓርቲ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አንሥተዋል።
በ2013ቱ ሀገራዊ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ መንግሥት መመሥረት የቻለ መሆኑን ጠቁመው፣ ፓርቲው ሀገራዊ አንድነትን እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በይበልጥ ለማጎልበት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ ማካተት መቻሉን ገልጸዋል።
በሚኒስትር ደረጃም በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ በማካተት እና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ከፓርቲ ክፍፍል በላይ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚሠራ ፓርቲ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ፓርቲው አካታችነት ላይ በሠራው ሥራ የሴቶችን አቅም በማጎልበት ለአመራርነት ማብቃቱን አቶ አደም ፋራህ በንግግራቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ካቢኔ 50 በመቶ በሴቶች የሚመራ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም የፆታ እኩልነት ላይ የተሠራው ሥራ ፍሬያማ መሆኑን ያመላክታል ሲሉ ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ካሉት የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ውስጥ 49 በመቶ የሚሆነው በወጣቶች መያዙንም አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ