Search

የፖለቲካ ስኬትን የምንለካው በምርጫ ድሎች ሳይሆን በዜጎቻችን ሕይወት ነው፡- አቶ አደም ፋራህ

ማክሰኞ ነሐሴ 06, 2017 170

የፖለቲካ ስኬትን የምንለካው በምርጫ ድሎች ሳይሆን በዜጎች ሕይወት ላይ በተሰሩ ተጨባጭ ማሻሻያዎች ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ።
አቶ አደም ፋራህ በጋና በተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል።
የፓርቲያችን ራዕይ ከፖለቲካ ዑደት ባለፈ የፖሊሲ ቀጣይነትን ተቋማዊ ማድረግ አስችሏል ያሉት አቶ አደም ፋራህ፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እየሰራን ይገኛል ብለዋል።
የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሦስት ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባቸውም አደም ፋራህ አመላክተዋል።
 
 
 
የሰላም፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ ንቁ ትብብር ለማድረግ የፓርቲዎችን ውይይት ተቋማዊ ማድረግ የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል።
በሁለተኛነት ወጣቶችን በትምህርት፣ በሥራ ፈጠራ እና በፖለቲካ ተሳትፎ ማበረታታት የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።
ለዘላቂ ዕድገት የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን፣ ታዳሽ ሃይልን እና ፈጠራን በመጠቀም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና ዲጂታል ሽግግሮችን ተግባራዊ ማድረግ ሶስተኛው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በአረንጓዴው አሻራ ተነሳሽነት ከ48 ቢሊዮን በላይ ዛፎችን በመትከል ኢኮኖሚያዊ ፣ አካባቢያዊ እና ተምሳሌታዊ ጥቅሞችን ተገኝተዋል ሲሉ አቶ አደም ፋራህ ገልፀዋል።
ታሪክ የሚዘክረን በማዕረጎቻችን ሳይሆን ጠንካራ ሀገርን፣ ፍትሃዊ ማህበረሰብን እና በእራስ የመተማመን መንፈስ ስንገነባ ነው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ከመከፋፈል ይልቅ ውይይትን፣ ከማግለል ይልቅ መደመርን፣ ከፉክክር ይልቅ አጋርነትን እንምረጥ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሴራን ታደሰ