Search

በበርካታ የምርጫ ክልሎች የድምፅ ማዳመር እና ቆጠራ ሂደቱ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

ቅዳሜ ግንቦት 29, 2018 11

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ ማዳመር እና ቆጠራ ሂደት አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት መግለጫ፤ በርካታ የምርጫ ክልሎች የማዳመሩን ሥራ አጠናቀው ውጤት ይፋ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ በተወሰኑ አካባቢዎች ግን የተለያዩ ተግዳሮቶች በማጋጠማቸው ምክንያት ሂደቱ መዘግየቱን አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚገኙ 29 የምርጫ ክልሎች ውጤታቸውን አጠናቀው ወደ ዋናው ማረጋገጫ ማዕከል መላካቸውን ቦርዱ ገልጿል።

በምርጫው ሂደት የተለያዩ ቅሬታዎች ለምርጫ ቦርዱ የቀረቡ ሲሆን ቦርዱ ለእነዚህ ቅሬታዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት፣ በተለይም የፓርቲ ወኪሎች በድምፅ ቆጠራው ላይ በአካል እንዲገኙ ከማድረግ አንጻር ጠንካራ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ሰብሳቢዋ አብራርተዋል።

በቀጣዮቹ ሁለት እና ሦስት ቀናት ውስጥ ሁሉም የምርጫ ክልሎች የማዳመሩን ሥራ አጠናቀው በምርጫ ክልላቸው ውጤት ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቦርዱ በመግለጫው አመላክቷል።