ኢትዮጵያ ከይፋዊ አበዳሪዎች ጋር የተጀመረው የውጭ ዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ መድረሱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 25ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የ2019 በጀት ዓመት መነሻ ዕቅድን ለውይይት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
የመንግሥትን የውጭ ብድር ጤናማ ለማድረግ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ስር የተጀመረው የዕዳ ሽግሽግ ሂደት በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በዋና ዋና የፋይናንስ መለኪያዎች ላይ የተደረሰውን ስምምነት መሠረት በማድረግ የመግባቢያ ሰነድ የተፈረመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከአብዛኞቹ አበዳሪዎች ጋር የሁለትዮሽ የዕዳ ሽግሽግ ስምምነቶች ተፈርሟል።
ከዩሮቦንድ እና ከሌሎች አበዳሪዎች ጋር የሚደረገው ድርድርም ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረቡን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ይህም በየዓመቱ ለዕዳ ክፍያ የሚውለውን የውጭ ምንዛሬ ጫና በመቀነሱ ለኢትዮጵያ የልማት ፋይናንስ ተጨማሪ ሀብት ለማዋል ማገዙን እና የሀገራችን የዕዳ ጫና ስጋት ወደ መካከለኛ ደረጃ ዝቅ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
በመጠናቀቅ ላይ ባለዉ 2018 በጀት ዓመት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ምርታማነት እና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን አቶ አሕመድ ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አማካኝነት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት መጀመሩን እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚከናወነውን የቢሾፍቱ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክትን በዋነኛነት ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካለፉት ዓመታት እጅግ የተሻለ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በዚህም መሰረት በ2019 በጀት ዓመትም የ10.1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚመዘገብ ግምት መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
በበረከት ሽመልስ