Search

በጅማ ከተማ ለልማት ተነሺዎች የተገነቡ 300 የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላለፉ

እሑድ ሰኔ 28, 2018 192

የጅማ ከተማ አስተዳደር 763 ሚሊዮን ብር በጀት ለልማት ተነሺዎች የገነባቸውን 300 ዘመናዊ የቁጠባ መኖሪያ ቤቶችን በትናንትናው ዕለት ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በምረቃው ወቅት እንዳሉት፣ አስተዳደሩ በርካታ ፕሮጀክቶችን በጥራት እና በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት እያዋለ ይገኛል።

300 የልማት ተነሺዎች የተላለፉት ቤቶችም ለኑሮ ተስማሚ እና ዘመናዊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፣ መንግሥት ከተሞችን በማዘመን የዜጎች ኑሮ ምቹ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

 

በከተማ መስተዳድሩ ለልማት ተነሺዎች የተገነቡት እነዚህ የቁጠባ መኖሪያ ቤቶችም የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል።

የመኖሪያ ቤቶቹ ተጠቃሚ የሆኑት የልማት ተነሺዎች፣ የተሰጧቸው ቤቶች መሠረተ ልማት የተሟላላቸው በመሆናቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በወሰኑ አውግቸው