Search

በታላቁ መድረክ የዓለምን ልብ የገዛችው ትንሿ ሀገር - ኬፕ ቬርድ

እሑድ ሰኔ 28, 2018 147

 

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከጠበቅነው በላይ አስገራሚ ክስተቶችን እና ድንቅ ታሪኮችን እያስተናገደ ይገኛል።

ታላላቅ የሚባሉት ሀገራት እና ከዋክብት ሲፈተኑ፣ ያልተጠበቁት ደግሞ የዓለምን ትኩረት ስበዋል።

ከነዚህም መካከል በሰፊው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ውኃ የተከበበችው፣ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር እና ስፋት ያላት ትንሿ ኬፕ ቬርድ ግንባር ቀደሟ ናት።

'ሰማያዊ ሻርኮቹ' በሚል ቅፅል ስም የሚጠራው የኬፕ ቬርድ ብሔራዊ ቡድን፣ በአፍሪካ ቀጣና ሲያደርግ የነበረው ቀስ በቀስ የማደግ ሂደት፣ ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ በዓለም መድረክ ላይ በድምቀት እንዲታዩ አድርጓቸዋል።

ትልልቅ ስም ያላቸውን ተጫዋቾች ሳይሆን፣ በትልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚጫወቱ ጀግኖችን ይዘው በመምጣት መላው የእግር ኳስ አፍቃሪውን ልብ በታላቅ አድናቆት መግዛት ችለዋል።

የዚህች አነስተኛ ደሴት ሀገር ቡድን ስኬት ምስጢር በዋናነት የማይበገረው የቡድን መንፈሱ ነው።

በኬፕ ቬርድ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ "እኔ" የሚል ስሜት አይታይም፤ ሁሉም ተጫዋቾች ለአንድ ዓላማ፣ ለሀገራቸው ባንዲራ እና ሕዝብ በጋራ ይዋጋሉ።

ከዚህም ባለፈ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እና ጠንካራ የተከላካይ መስመራቸው የቡድኑ ዋነኛ መለያዎች ናቸው።

የዚህ ሁሉ ጥንካሬ የጀርባ አጥንት እና ዋነኛ ምሰሶ ደግሞ "ቮዚኛ" በሚል ስሙ የሚታወቀው ግብ ጠባቂው ጆሲማር ጆዜ ኤቮራ ዲያዝ ድንቅ ብቃት ነው።

ቮዚኛ በግብ ክልሉ ውስጥ የሚያሳየው መረጋጋት እና በሚገርም ቅልጥፍና የሚያድናቸው ኳሶች፣ ከተጋጣሚ አጥቂዎች ጫና በላይ በራሱ ተጫዋቾች ላይ የፈጠረው የሥነ-ልቦና ጥንካሬ እጅግ የላቀ ነው።

ኬፕ ቬርድ በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ በርካታ በታሪክ የሚዘከሩ ገድሎችን መሥራት ችላለች።

የሰማያዊ ሻርኮቹ እና በተለይም የግብ ጠባቂው የቮዚኛ አስደናቂ ብቃት የዓለም ታላላቅ ሚዲያዎች አጀንዳም ሆኖ ሰንብቷል።

አልጀዚራ ኬፕ ቬርድ 2024 የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነችውን ስፔንን ያለምንም ግብ 0-0 በአቻ ውጤት የገታችበትን ጨዋታ ሲዘግብ፣ ውጤቱን "ታላቅ ድንገተኛ ክስተት" በማለት ገልጾታል።

ሚዲያው የኦፕታ (Opta) ስታቲስቲክስን ጠቅሶ እንዳስነበበው፣ ስፔን 27 ሙከራዎችን ብታደርግም በቮዚኛ እና በተከላካዮቹ ጥንካሬ የኬፕ ቬርድን መረብ መድፈር አልቻለችም።

ይህ የቮዚኛ ግላዊ ስኬት ምን ያህል አስገራሚ እንደነበር ስትራይቨር (Striver) የተሰኘው የስፖርት ሚዲያ በሰፊው አጉልቶታል። ስትራይቨር ባወጣው ዘገባ፣ ቮዚኛ ከስፔን ጋር በነበረው ጨዋታ 7 ኳሶችን ያዳነ (saves) ሲሆን፣ 68 ጊዜ ኳስን መንካቱን ዘግቧል፤ ይህም 1988 ወዲህ በዓለም ዋንጫ አንድ ግብ ጠባቂ ያስመዘገበው ከፍተኛው የኳስ ንክኪ ነው።

የእንግሊዙ ታዋቂ ጋዜጣ ጋርዲያን በበኩሉ፣ ኬፕ ቬርድ በአርጀንቲና 3-2 በተሸነፈችበት እና በጀግንነት ከውድድሩ በተሰናበተችበት ጨዋታ ላይ የነበራትን ብቃት በማድነቅ "ትንሿ ኬፕ ቬርድ ትኩረቱን ሁሉ ከአርጀንቲና ነጠቀች" ሲል ጽፏል።

የቮዚኛ ጀግንነት የአርጀንቲናን ጥቃት ደጋግሞ በመመለስ እና ጨዋታው ወደ ጭማሪ ሰዓት እንዲያመራ በማድረግ በዓለም ዋንጫው ያልተጠበቁ የምንግዜም ጀግኖች ተርታ ቦታውን እንዳጸናለትም ጋዜጣው ዘግቧል።

ከጨዋታው በኋላ የቡድኑ አሰልጣኝ ቡቢስታ "ትንሽ ሀገር ብንሆንም ከማንኛውም ቡድን ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ እንደምንችል አሳይተናል... በዚህ ውድድር ባሳካነው ነገር እጅግ እንኮራለን" በማለት የተናገሩትን ኩራት የተሞላበት ቃል ጋርዲያን አጋርቷል።

ጎል የተሰኘው የስፖርት ድረ ገጽ፣ኬፕ ቬርድ 90 ደቂቃ አንድም ሽንፈንት ሳታስተናግድ ዓለም ዋንጫ ጉዞዋን አጠናቅቃለችሲል የትንሿን ሀገር ድንቅ ብቃት አወድሷል።

አዎ፣ ኬፕ ቬርድ በዓለም ዋንጫ ጉዞዋ ባደረገችው የምድብ ጨዋታዎች ከስፔን ጋር 0 0 ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር 0 0 ከዩጋጓይ ጋር 2 2 ነው የተለያየችው።

በጥሎ ማለፍ ጨዋታውም ከአርጀንቲና ጋር በመደበኛው 90 ደቂቃ ጨዋታ 1 1 በሆነ ውጤት አጠናቅቃ፣ በተጨማሪ 30 ደቂቃ ላይ ነው 3 2 ተሸንፋ ከዋንጫው የተሰናበተችው።

እግር ኳስ ከሜዳ ላይ ፉክክር ባለፈ የተስፋ፣ የእምነት እና የትጋት ተምሳሌት መሆኑን የኬፕ ቬርድ ብሔራዊ ቡድን በተግባር አሳይቶናል።

በአንድነት ከተሠራ እና እንደ ቮዚኛ ያሉ ጀግኖች በቁርጠኝነት ከተሰለፉ የትኛውንም ተራራ መውጣት እንደሚቻል አይተናል።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የትኛውም ደረጃ ላይ ደርሰው ቢሰናበቱም፣ ለዓለም ሕዝብ ያስተላለፉት የፅናት መልዕክት ግን ለዘመናት በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።

በዮናስ በድሉ