“እንዴት እንዲህ ያለው የሚጎረብጥ ሀሳብ በምክክር አደባባይ ይነሳል?” ብለው ይሰጋሉ? ግን ቆይ... ሀሳብ ተደብቆ በጠብመንጃ ድምፅ ከሚገለፅ፣ አደባባይ ወጥቶ በጠረጴዛ ዙሪያ መሞገቱ የሁላችንም ትልቁ ድል አይደለምን?
በሀገራችን የፖለቲካና የማህበራዊ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት የቆዩት መዋቅራዊ ስብራቶችና የትርክት ቅራኔዎች፣ በሰከነ አደባባይ ከመሞገት ይልቅ በድብቅና በትህትና መካካድ ተሸፍነው መቆየታቸው ይታወቃል።
ይሁንና አሁን በመካሄድ ላይ የሚገኘው ታላቁ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ ይህንን አስተሳሰብ በጽኑ መሠረት ላይ እየቀየረው ይገኛል።
በአንድ የጋራ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የሚነጋገሩ ወገኖች፣ ላለፉት ዘመናት ሀገራችንን ሲፈታተኑ የቆዩ መዋቅራዊ ስብራቶችንና የታሪክ ቅራኔዎችን በመተኪያ የሌለው የውይይት ባህል ለመጠገን በጋራ እየተጉ ይገኛሉ።
አንድን ሀገር ከጽኑ ውድቀት የሚያድነው ልዩነቶችን መሸሸግ ሳይሆን፣ አውጥቶ በግልጽ መሞገት ነው። በምክክር ሂደቱ ውስጥ የሚነሱቱ እሳቤዎችና የሚካሄዱት ሞቅ ያሉ ክርክሮች የሀገራችንን ድክመት ሳይሆን፣ የህብረተሰቡን የፖለቲካ ብስለትና የሂደቱን ጤናማነት የሚያሳዩ ናቸው።
ለዘመናት ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ ዕድል ባለመኖሩ ምክንያት፣ ተደብቀው በጠመንጃና በኃይል ይገለፁ የነበሩ ቅሬታዎች ዛሬ አደባባይ ወጥተው በጠረንጴዛ ዙሪያ መሞገታቸው እራሱ ትልቁ ሀገራዊ ድላችን ነው። ሀሳብ በጠረንጴዛ ዙሪያ ሲሸነፍ ሀገር ታሸንፋለች፤ በጠመንጃ ሲገለፅ ግን ሁሉም ተሸናፊ ይሆናል።
በጠረንጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ በሰከነ ውይይት መፈታት ይችሉ የነበሩ ጥቃቅን አለመግባባቶች፣ ተገቢ ያልሆነ የሰው ሕይወትና የሀብት መስዋዕትነት እንዲከፈል ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አሁን ግን ከመላ ኢትዮጵያ የተውጣጡ ሁሉ እና የባህል አባቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጋራ መምከራቸው፣ የቆዩ ስብራቶችን በጥበብ ለመጠገን አዲስ መንገድ ከፍቷል።
በምክክሩ የሚነሱ የሀሳብ ልዩነቶችን በቅንነት ተቀብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር፣ ለዘመናት የቆዩ አላስፈላጊ መስዋዕትነቶችን በማስቀረት ዘላቂ አብሮነትን ለማረጋገጥ ፍቱን መፍትሔ ያመጣል።
የሀሳብ ልዩነቶች በግልጽ መድረክ ላይ መስተናገዳቸው የሀገር ግንባታ የጋራ ትርክት ለመፍጠርና የህብረ-ብሔራዊ አንድነት እሳቤን ለማጎልበት መሠረት ይሆናል።
ልዩነቶችን እንደ ስጋት ከመቁጠር ወጥተን እንደ ውበትና እንደ ጤናማ የውይይት ሂደት መቀበል ስንችል፣ ለተተኪው ትውልድ የተረጋጋች፣ የበለፀገችና በውይይት ባህል የምትመራ ሀገርን ማስተላለፍ እንችላለን።
መወያየት፣ መሞገትና በጠረንጴዛ ዙሪያ መደመጥ የዛሬው ትውልድ ከነገዋ ኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘው ህያው የጋራ ኃላፊነት ነው። ሀሳብ በጠመንጃ ሳይሆን በጠረንጴዛ ዙሪያ መሞገቱ የሁላችንም ትልቁ ድል ነው።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: