የመቶ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠሩት ሁለት ቻይናውያን እህትማማቾች ከብዙ አሥርተ ዓመታት መለያየት በኋላ በስተመጨረሻ በቪዲዮ ጥሪ ዳግም ተገናኝተዋል።
እህትማማምቹ የሚኖሩት አንዷ በታይዋን፣ ሌላኛዋ ደግሞ በቻይና ምሥራቃዊ ግዛት በጂያንግሱ ግዛት ሲሆን የተገናኙበት መንገድ ታዲያ የብዙዎችን ልብ ነክቷል።
ዳግም መገናኘት እንደማይችሉ አምነው ኑሯቸውን ሲገፉ የቆዩት እነዚህ የዕድሜ ባለፀጎች፣ ምስጋና ለማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና ለፖሊሶች ይሁንና በስተመጨረሻ በበይነ መረብ መገናኘት ችለዋል።
በተለይ ከሄናን ግዛት የመጣች ወጣት ተፅዕኖ ፈጣሪ እህትማማቾቹን በማገናኘት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቷ ነው የተነገረው።
ተፅዕኖ ፈጣሪዋ ወጣት ከሁለቱ እህትማማቾች መካከል ታላቋ እህት ዌን ሱን በመቅረፅ ለረጅም ጊዜ የናፈቀቻትን እህቷን ለማግኘት ያላትን ፍላጎት ስትናገር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ታጋራለች።
ተንቀሳቃሽ ምሥሉም በፍጥነት ተሰራጭቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ፍንጭ እና በአካባቢው ፖሊስ ድጋፍ አማካኝነት በመጨረሻም በጂያንግሱ ግዛት ያለችውን ታናሽ እህቷን ዌን ኩዋንማይን ማግኘት ችለዋል።
ለብዙ ዓመታት ሳይገናኙ የቆዩት እህትማማቾቹ ፊት ለፊት ሲተያዩ በዕንባ እና በናፍቆት ልብ በሚነካ መንገድ ተነጋገሩ።
ስሜታቸው ከእነሱ አልፎም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተመለከታቸውን ሁሉ ስሜት ነክቷል።
የመጀመሪያው ድልድይ እንደገና በመገንባቱ፣ ቤተሰቦች እና ባለሥልጣናት የእህትማማቾቹን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ፊት ለፊት የመገናኘት ተስፋ እውን ለማድረግ እየሞከሩ ነው ሲል ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት።
ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎነት መጠቀም በተግባር ሲሉም ብዙዎች መደሰታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
በሴራን ታደሰ