ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን።
ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፤ የመሸጋገሪያ ወቅት ነው። “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ። በሌላ በኩልም “ቡኮ/ሊጥ” ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት “ሙልሙል” የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል።
ጅራፍ
ጅራፍ መገመድ እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው።
የመጀመሪያው የኢየሱስ ክርስቶስን ግርፋት እና ሞቱን የሚታሰብበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የጅራፉ ድምፅ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፣ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሳል።
ችቦ
ችቦ የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት መገለጥን የሚያመለክት ነው። በመሆኑም ይህን ለማሰብ ችቦ ተለኩሶ በዓሉ ይከበራል። የዚህ ትውፊታዊ አመጣጥ ደግሞ በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተው ወላጆች ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ለመዘከርም ነው። የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርዓያ ምሳሌ ብርሃን መሆኑን ያሳያል። በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል።
ሙልሙል
በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል። ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው። በየቤቱ “ቡሄ” እያሉ ለሚሄዱ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ አለ። ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም። ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ሲሆኑ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት “የምሥራች” ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ እንደሆነ የሃይማኖት አባቶች ይገልጻሉ።
በጥበቡ አስፋው