የሰው ልጅ ታሪክ ሲጻፍ ማኅበራዊ ትስስር፣ መከባበር እና የጋራ ኑሮ የጀመሩባቸውን ምዕራፎች የሚጠቁሙ ልዩ ምልክቶችን ያስቀምጣል።
ኢትዮጵያ የምድረ ቀደምት እና የቡና መገኛ በመሆን ለዓለም አቀፍ ባህል ያበረከተችው አስተዋጽኦ እንዲሁ በታሪክ ምዕራፍ ሰፍሯል።
ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም የጣዕም፣ የንቃት እና የሰላም ምንጭ ሆኖ የዘለቀው ቡናችን ከዘመናት ማኅበራዊ ሕይወታችን ጋር ተዋህዶ የቆየ የክብር መታወቂያችን ነው።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ ቡና ከመጠጥነት በላይ የሰዎች ግንኙነት የሚጠናከርበት፣ የልብ ሐሳብ የሚንሸራሸርበት እና ማኅበራዊ ትስስር የሚጸናበት ጥልቅ ሥርዓት ነው።
ማኅበረሰባችን ትልቅ ክብር ሲሰጥ፣ እንግዳ ሲቀበል ወይም የደስታ እና የሐዘን ማኅበራዊ መድረኮችን ሲያዘጋጅ "ቡና ጠጡ" የሚለው ቃል የፍቅር፣ የአክብሮት እና የሰላም ጥሪ መሆኑ ይታወቃል።
ቡና የኢትዮጵያ አረንጓዴ ወርቅ እና የባህል መታወቂያ ሆኖ የኖረ ቢሆንም፣ ከሀብቱ መገኛነቷ አንጻር ከዓለም አቀፍ የገበያ ሰንሰለት ማግኘት የሚገባትን ያክል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሳያታገኝ ቆይታለች።
ዛሬ ላይ ግን ታሪክ ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ እና በምጣኔ ሀብት ልማት ያስመዘገበችው ድል ቡናን ዳግም ከፍ ያለ ክብር እንዲጎናጸፍ አድርጎታል።
አሁን ላይ ቡና የሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ምንጭ በመሆን የኢኮኖሚያችን ማዕከላዊ ምሰሶ ከመሆን አልፎ ምልክታችን ሆኗል።
ኢትዮጵያ በ2027 ለምታስተናግደው 32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ስትዘጋጅ፣ የቡና መገኛነቷን የጉባኤው ዋና ማኅበራዊ እና ባህላዊ መደብ አድርጋ መምረጧ የሰመረ የዲፕሎማሲ ሥራ ነው።
ዓለም አቀፍ መሪዎችን እና ልዑካንን "ኑ ቡና ጠጡ" እያለች ስትጋብዝ፣ በጉባኤው ጠረጴዛ ላይ የሚነሱትን ውስብስብ የአየር ንብረት ቀውስ ውይይቶች በአቦል፣ ቶና እና በረካ የመተሳሰብ መንፈስ እንዲፈቱ ጥሪ እያቀረበች ትገኛለች።
ለዚህ ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንግዶቿን በቡና ጥሪ የምታስተናግደው ኢትዮጵያ ዓለም ለተጨነቀበት የአየር ንብረት ለውጥ በተግባር ያመጣቻቸውን ዐበይት መፍትሔዎች ለዓለም ማኅበረሰብ ታካፍላለች።
ሀገራችን በመሬት ላይ ባከናወነቻቸው ተጨባጭ እርምጃዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ጽናት አርአያ ሆናለች።
በተለይም የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄን በመጀመር የደን ሽፋኗን ማሳደጓ፣ ከ90 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይሏን ከንጹሕ የውኃ ምንጮች መሆኑ፣ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን በማገድ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በስፋት ወደ ሥራ ማስገባቷ እንዲሁም በምግብ ዋስትና እና በመስኖ ልማት የተረጋገጡ ስኬቶችን ማስመዝገቧ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምታካፍላቸው ዐበይት ተሞክሮዎች ናቸው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ መምጣት እና የቡና መዓዛ ከሰላም እና ከዘላቂ ልማት ትርክት ጋር ተጣጥሞ መቅረቡ ለአፍሪካ የአየር ንብረት የፍትሕ ድምፅ ትልቅ ከፍታን ይሰጣል።
የአፍሪካ አህጉር ለዓለም አቀፍ የልቀት መጠን ያላት አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ ሆኖ ሳለ የሚደርስባትን ተጽዕኖ በዘላቂ አረንጓዴ ልማት ለመመከት የምታደርገው ጥረት በCOP32 በሰፊው የሚንጸባረቅ ይሆናል።
በተግባር የተረጋገጠውን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ይዛ ወደፊት የገሰገሰችው ኢትዮጵያ ከቡናዋን መዓዛ ጋር ዓለምን ወደ እውነተኛ ትብብር እና ፍትሐዊ የፋይናንስ ሥርዓት እየጠራች ትገኛለች።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: