ኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር አካባቢ በጂኦግራፊ፣ በታሪክ እና በባህል የተጋመዱ፣ ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።
ትውልዱ የባሕር በር ጥያቄ ማንሳቱን አንዳንዶች እንደ ወቅታዊ የፖለቲካ አጀንዳ ሊያስመስሉት ቢሞክሩም፣ እውነታው ግን ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር የሺህ ዘመናት ታሪካዊ ቁርኝት እና የማይነጣጠል የጋራ ሕልውና ያላቸው መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ንግድና ግንኙነት (ዲፕሎማሲ) ያላት ጥንታዊ ገናና ታሪክ የተመሠረተው በቀይ ባሕር የንግድ መስመር ላይ ነው።
ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የሚታወቀው የአክሱም ስልጣኔ አዶሊስን እና ሌሎች የቀይ ባሕር ወደቦቹን በመጠቀም ከሮማ፣ ከግሪክ፣ ከሕንድ፣ ከሰሜን ምሥራቅ አፍሪካና ከደቡብ አረቢያ ጋር ግዙፍ የባሕር ንግድ ልውውጥ ያደርግ ነበር።
ለሺህ ዘመናት ይህን ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር በባለቤትነት ያስተዳደረችው ኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ ቀንድ እስከ መካከለኛው ምስራቅ የዘለቀውን የኢኮኖሚ እና የባህል ልውውጥ ትመራ ነበር።
በዚህ ረጅም ታሪካዊ ሂደት ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ መስኮት ብቻ ሳይሆን አህጉሪቱን ከቀሩት የዓለም ክፍሎች ጋር የሚያስተሳስር ዋናው የዲፕሎማሲ ድልድይ ነበር።
ሆኖም ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት ያጋጠመን ሀገራዊ የፖለቲካ ስብራት ከዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ ሴራዎች ጋር ተዳምሮ ያለምንም ሕጋዊ ሂደት የባሕር በራችን ተዘግቶብናል።
ይሁን እንጂ ይህ ታሪካዊ ስህተት ኢትዮጵያውያን ከቀይ ባሕር ጋር ያላቸውን ለሺ ዘመናት የዘለቀ የባህል ትስስር ሊፍቀው አይችልም፤ ሕጋዊነት በጎደለው ሂደት ካርታ ቀይሮ አንድን ሀገር ከባሕር በማግለል ብቻ የሚቀየር ቋሚ የተፈጥሮ ሕግም የለም።
ለእኛ ኢትዮጵያውያን ወደ ቀይ ባሕር መመለስ ማለት ወደ ታሪካዊ ማንነታችን እና የኢኮኖሚ ነጻነታችን መመለስ ማለት ነው።
የመደመር ስልጣኔን ያህል #ታላቅርዕይ ለሰነቀ የ130 ሚሊዮን #ትልቅሕዝብ #ትልቅሀገር ባሕር በር አልባ መሆን ለብልጽግናው ማነቆ፣ ለደህንነቱም ስጋት ነው።
ቀደምት አባቶቻችን ያስረከቡንን ሁለንተናዊ ነጻነት እና ሉዓላዊነት በሰለጠነ ዲፕሎማሲ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ በማስከበር በተራችን ለቀጣይ ትውልድ ማውረስ የሁላችንም ታሪካዊ አደራ ነው።
ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር የማይነጣጠል የጋራ ሕልውና ያላቸው ለመሆኑ ታሪክ ራሱ ምስክር ነው። ከጥንታዊው የአክሱም ስልጣኔ እስከ ዛሬው የመደመር ስልጣኔ፣ ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ማንነቷ፣ የደህንነቷ ካስማ እና የሁለንተናዊ ብልጽግናዋ ሞተር መሆኑን ትውልዱ አበክሮ ተገንዝቦታል።
ይህ ትውልድ የቀይ ባሕር ትውልድ ነው፤ ሕጋዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብቱ እስኪመለስለት እጅ ለእጅ በመያያዝ ፍትሐዊ ጥያቄውን አጠናክሮ ይቀጥላል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: