የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሀጽዮን በአንታሊያ ቱርክ እየተካሄደ ባለው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP31) ከኤንዲሲ አጋርነት ድርጅት (NDC Partnership) ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ዶ/ር ፓብሎ ኤ. ቪዬራ ጋር በኢትዮጵያ ፓቪሊዮን የሁለትዮሽ ውይይት አካሄዱ። ውይይቱ ኢትዮጵያ በኅዳር 2020ዓ.ም ለምታስተናግደው 32ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ዝግጅት አንጻር ስትራቴጂያዊ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከ2009 ጀምሮ የድርጅቱ አባል በመሆን እያገኘች ላለው የረጅም ጊዜ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ድጋፉ በተለይም በብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅድ (NDCs) እና የረጅም ዘመን የዝቅተኛ የልማት ስትራቴጂ (LT-LEDS) ሰነዶች ዝግጅትና ትግበራ፣ በአየር ንብረት አስተዳደር፣ በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በግልጽነት ሥርዓት እና በንጹህ ኃይል ዘርፎች የተገኘውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያን የNDC 3.0 ትግበራ (NDC 3.0 implementation) ፣ የአየር ንብረት ፋይናንስና ኢንቨስትመንት ማሰባሰብ፣ የካርቦን ገበያ ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አቅም ማጠናከር እንዲሁም ተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ ትብብሩን ወደ ተሻለ ስትራቴጂያዊ ደረጃ የማሸጋገር አስፈላጊነት በሁለቱም ወገኖች ተጠቁሟል።
ዶ/ር ፓብሎ በበኩላቸው ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የረጅም ጊዜ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከርና ለCOP32 ዝግጅት ድጋፉን ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የሰው ዘር መገኛ፣ የፅናት እና የተስፋ ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን አየር ንብረት ጉባኤ ለማስተናገድ የምታደርገውን ሀገራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሙሉ እና ትክክለኛ የጉባኤውን መረጃዎች ከምንጩ ለማግኘት ሁልጊዜም የኮፕ-32 ይፋዊ ድረ-ገጽ https://cop32ethiopia.et/ ይጠቀሙ።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: