የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የኦሮሚያ ክልል አጎራባች ወረዳዎች የጸጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በአሶሳ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እድሪስ መሐመድ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን የአብሮነት እሴት ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም የሰላም እና አንድነት የማይሹ ጸረ-ሰላም ኃይሎች በሕዝቦች መካከል ልዩነት ለመፍጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በማክሸፍ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በቅርቡ በአሶሳ ዞን ቡልደግሉ ወረዳ ቤልፀሪ (ዳለቲ) ቀበሌ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ሕዝቡን የማይወክል ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መሆኑን በማንሳት አውግዘዋል።
የምዕራብ ኦሮሚያ ክላስተር ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ደረጀ ባይሳ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሕዝቦች በጋብቻ፣ በባህል እና በታሪክ የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ይህንን ጥልቅ ወንድማማችነት የሚሸረሽሩ ችግሮችን በጋራ በመመከት የሕዝቦቹን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በአዋሳኝ አካባቢዎች በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በጽኑ በማውገዝ መንግሥት በጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመልስ እና በቅንጅት እንዲሠራ ጠይቀዋል።
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የሁለቱ ክልሎች አጎራባች ወረዳ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በነስረዲን ሀሚድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: