Search

የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ የተጀመረው ርብርብ

ዓርብ ኅዳር 04, 2019 99

በኢትዮጵያ በተለይም በዋና ዋና ከተሞች በፍጥነት እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥር እና የከተሜነት መስፋፋት የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጎታል።

መንግሥት መሠረታዊ የዜጎች ጥያቄ የሆነውን የቤት ጥያቄ ለመመለስ የአምስት ዓመት ዕቅድ አውጥቶ የቤት ልማትን እንደ ዋነኛ የልማት አጀንዳ ይዞ እየሠራ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙ ቤቶችን በጎበኙበት ወቅት፣ "በአምስት ዓመታት ውስጥ ቤቶችን ገንብተን ለማስረከብ ለሕዝባችን ቃል ገብተናል፤ ይህንንም ቃላችንን በተግባር ለማረጋገጥ ቀን ከሌት ያለ እረፍት እየተጋን እንገኛለን" በማለት ገልጸዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት መንግሥት በከተሞች አካባቢ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የያዘውን ትኩረት እና የአፈጻጸም አቅጣጫ የሚያሳይ ነው።

ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ "ቀን ከሌት ያለ እረፍት" የመሥራት ባህልን ማዳበር እንደ ዋና ስልት አስቀምጦ እየሠራ የሚገኘው የመደመር መንግሥት፣ ከዚህ ቀደም በግንባታ ዘርፍ ይስተዋሉ የነበሩ የመጓተት ችግሮችን ለመቅረፍ አልሞ በከፍተኛ ፍጥነት እየሠራ ነው።

የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ከአካባቢ ጥበቃ እና ከከተማ ውበት ሥራዎች ጋር ተሳስረው እንዲከናወኑ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በዚሁም ሰፊውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የመንግሥት አቅም ብቻ በቂ ባለመሆኑ በመንግሥት እና በግል ዘርፍ አጋርነት የግል ባለሀብቶች እና የሪል እስቴት አልሚዎች በዘርፉ በስፋት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የቤት ግንባታ ፕሮግራሙ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መሠረት ከተሳካ በርካታ ዜጎችን የቤት ባለቤት ከማድረግ ባለፈ በግንባታው ዘርፍ ለበርካታ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። በተጨማሪም የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ያነቃቃል።

በሌላ በኩል ይህንን ትልቅ ዕቅድ በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት እና የዋጋ ንረት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነት እንዲሁም የመሬት አስተዳደር እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ቅንጅት በትኩረት ሊፈቱ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

በተለይም የሚገነቡ ቤቶች ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የመክፈል አቅም ያገናዘቡ እንዲሆኑ ማድረግ ሌላው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑም ይጠቀሳል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተገለጸው በአምስት ዓመት የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በመንግሥት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፣ ለዕቅዱ ስኬታማነትም በየደረጃው ባሉ አስፈጻሚ አካላት ቅንጅት እና በተጀመረው የሥራ ፍጥነት ቀጣይነት ባለው መንገድ ማከናወን ይጠበቃል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: