ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የጉባ ብስራቶች አንዱ የሆነው እና በብሔራዊ ደረጃ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የታቀደውን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ፣ የግብዓት አቅርቦትን ብቻ ሳይሆን ዜጎች እየኖሩባቸው የሚከፍሉባቸው የፋይናንስ ሥርዓቶች እየተዘረጋ መሆኑን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባታ ሂደት ላይ የምትገኝ እና ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ፍላጎት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ የቤት ልማት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስታውሰዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ የመጀመሪያው ትኩረት ለግንባታ የሚያስፈልጉ እንደ ብረት፣ መስታወት እና ሴራሚክ ያሉ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ሀገር ውስጥ የማምረት አቅም ማሳደግ ነው።
ሁለተኛው የፋይናንስ አቅርቦት ሲሆን፤ ሰው ቤት ስለተገነባ ብቻ በቀላሉ ሊገዛ ስለማይችል ፈንድ በማደራጀት እና ከባንኮች ጋር በመተባበር ዜጎች ቤቱን የግላቸው አድርገው እየኖሩበት የሚከፍሉበት የብድር (ሞርጌጅ) ሥርዓት እየተዘረጋ ይገኛል ብለዋል።
ሦስተኛው የትኩረት አቅጣጫ ግንባታውን በመንግሥት እና በግል አጋርነት (PPP) ማከናወን መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ከ100 ሺሕ በላይ ቤቶች ግንባታ ተጀምሮ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አብዛኞቹ ግንባታዎች ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እየተጠናቀቁ መሆኑን ጠቁመው፣ የእነዚህ 100 ሺሕ ቤቶች ግንባታ ሲጠናቀቅ ፕሮጀክቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚሰፋ አረጋግጠዋል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: