Search

ከጎደለ ላይ ቆርሶ መስጠት - የደሃውን እንባ የሚያብሰው የዘመኑ አርበኝነት

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 111

የሺዎች እናት ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና እና የሜቄዶኒያው መሥራች ቢኒያም በለጠ በርካታ ልባቸው የተሰበረ፣ የወደቁና ጧሪ ያጡ ወገኖችን ደግፈው በማቆም የሰብአዊነትና የአርበኝነትን ትርጉም በተግባር ጽፈዋል።

እነዚህ ብርቅዬ ዜጎች ይህን ታላቅ ገድል ሲፈጽሙ በሀብት ክምችት፣ በጤናም ሆነ በትምህርት ደረጃ ከብዙኃኑ የሀገራችን ልሂቃንና ዜጎች የተሻለ ምቹ ሁኔታ አልነበራቸውም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሁለቱን ተምሳሌቶች ሕይወት እንደ መነሻ በማንሳት በአንድ ወቅት እንዳስገነዘቡትም፣ የዚህ ዘመን አርበኝነት ሲመችና ሲተርፍ ብቻ የሚከወን የቅንጦት ተግባር ሳይሆን ከጎደለ ላይ ቆርሶ በመስጠትና ለሰው ልጅ ክብር ያለ ቅድመ ሁኔታ በመቆም የሚገለጽ የሕይወት መርህ ነው።

የሰብአዊ ከፍታ የመጨረሻው ደረጃም የሀገር ፍቅርን ከሕዝብ ወገንተኝነትና ከፍትሕ ጋር ያዋሃደው እውነተኛ አርበኝነት ነው።

በመታመን፣ በመውደድ፣ በመሰጠት፣ በመጣበቅና በመከላከል ምሰሶዎች ላይ የሚቆመው ይህ እሴት፤ ከክልልና ከሀገር ድንበር ተሻግሮ ለሰው ዘር ሁሉ ሰላምንና ፍትሕን የሚመኝ የሞራል ልዕልና አለው።

ይህም በግጭት መካከል እርጥብ ሳር ይዘው የሕዝብን ሕይወትና ሀብት በታደጉት የጋሞ የሰላም አባቶች፣ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ባስጠሩት የጥበብና የስፖርት ጀግኖች እንዲሁም የወገንን ቁስል በፈወሱ በጎ አድራጊዎች ሕይወትና ተግባር ውስጥ ጎልቶ ይታያል።

ቀደምት አባቶቻችን በፀረ-ኮሎኒያል ተጋድሎ ለአፍሪካ የነጻነት ፋና ወጊ እንደሆኑት ሁሉ፣ የዛሬው የመደመር ትውልድም በኅብረትና በአርበኝነት ድህነትንና ልመናን ታሪክ ያደረገች የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ አደራ ተጥሎበታል።

የመደመር እሳቤ የተበታተኑ አቅሞችን በማሰባሰብና ጉድለቶችን በመሙላት፣ ግለሰባዊ በጎነትን ወደ ሀገራዊ የልማት አርበኝነት ከፍ አድርጎታል።

ለዚህም ዳግማዊ ዓድዋ የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በጽናት ማጠናቀቅ መቻሉና በመደመር እሳቤ የተከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ሕያው ምስክሮች ናቸው።

ይህ ትውልድ የሀገርን ሉዓላዊነት በኢኮኖሚ ነጻነት የማጽናት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

በመደመር እሳቤ የልማት ሁሉ ማዕከልና መዳረሻ ሰው በመሆኑ፣ የዘመኑ አርበኝነት በግዙፍ ግንባታዎች ብቻ ሳይወሰን ዘርና ቋንቋ ሳይለይ የደሃውን እንባ በሚያብሱ ሰው ተኮር ተግባራት ይገለጻል።

በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች ተስፋና አቅም የሰጠው የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር፣ በዝናብና በፀሐይ ይፈተኑ የነበሩ የአቅመ ደካሞችንና የአረጋውያንን ቤቶች የማደስ ንቅናቄ እንዲሁም በበዓላትና በችግር ጊዜያት የሚከወነው የማዕድ ማጋራት ባህል የዚሁ ሰብአዊ አርበኝነት ተጨባጭ ፍሬዎች ናቸው።

እነዚህ ሰው ተኮር ልማቶች የዜጎችን ሰብአዊ ክብር የሚመልሱ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን የሚያሰፍኑና የእርስ በርስ መተሳሰብን የሚያጠናክሩ የመደመር ትሩፋቶች ሆነዋል።

በመሆኑም የዘመኑ አርበኝነት የሚጠይቀው የሰውን ሕይወት በሚለውጥ ተጨባጭ ሥራ በታሪክ መታወስን ነው።

እነ ዶክተር አበበች ጎበና እና ቢኒያም በለጠ በግል ጥረታቸው ያቀጣጠሉት የሰብአዊነት ችቦ፣ ዛሬ በመደመር እሳቤ ተቋማዊና ሀገራዊ ቅርጽ ይዞ በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ ብርሃን እየፈነጠቀ ይገኛል።

ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከሰው ተኮር የልማትና የድጋፍ ሥራዎች ጋር አስተሳስሮ መጓዝ የቻለው ይህ ትውልድ፣ የመከፋፈል አጥሮችን በማፍረስና ለወገን ደራሽነቱን በተግባር በማስመስከር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ያደርጋል።

ለሀገር መቆም ማለትም ለዜጎች ክብር መትጋትና ከራስ አልፎ ለትውልድ የሚሻገር የፍቅር፣ የልማትና የኅብረት አሻራ ማኖር መሆኑን የዛሬዋ ኢትዮጵያ ጉዞ በግልጽ ያረጋግጣል፡፡

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: