Search

የከበሩ ማዕድናትን ያከበረችው ኢትዮጵያ

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 118

በማዕድን ማውጣትና ማጣራት ሂደት ውስጥ እንደ ወርቅ ያሉ የከበሩ ማዕድናትን ከማምረት ጋር ተያይዞ በርካታ መጠን ያላቸው ቆሻሻዎችና ተረፈ-ምርቶች ይመረታሉ።

ከእነዚህም መካከል ትርፍ አፈር፣ ድንጋይ እንዲሁም ኬሚካሎችና ከባድ ብረቶች የተቀላቀሉባቸው ዝቃጮች ይገኙበታል።

ከዚህ ቀደም እነዚህ ተረፈ-ምርቶች በአግባቡ ሳይያዙ እንደ ተራ ቆሻሻ በመጣላቸው አካባቢን ከመበከል ባለፈ፣ በውስጣቸው የተደበቁ እንደ ታንታለም ያሉ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ማዕድናት እና ጥቃቅን የወርቅ ብናኞች በከንቱ ይባክኑ ነበር።

ይህ ደግሞ ለሀገራችን የከበሩ ማዕድናት ሊሰጥ ከሚገባው ተገቢ ስፍራ አንፃር ትልቅ ክፍተት ፈጥሮ ቆይቷል።

ይህንን የሀብት ብክነት እና የአካባቢ ብክለት በዘላቂነት በመቀየር ከቆሻሻነት ወደ ውድ ሀብት ለመለወጥ በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የተገነባው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ሰፊ በር ከፍቷል።

ፋብሪካው እነዚህን ተረፈ-ምርቶች በዘመናዊ የሳይንስና የቴክኖሎጂ አሰራር በመቃኘት፣ እንደ ታንታለም ያሉ ማዕድናትን በትክክል በመለየት ለጥቅም በማዋል ሀገራችን ለከበሩ ማዕድናት የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት በተግባር አሳይቷል።

በዚህም ኢትዮጵያን ጥሬ ዕቃ ከመላክ አውጥቶ እሴት የተጨመረባቸውን ማዕድናት ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ በማስቻል የውጭ ምንዛሪ ገቢን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ ይገኛል።

ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ፋብሪካው በየዕለቱ ላባቸውን የሚያፈሱት ታታሪ የወርቅ አውጪዎች እና አንጥረኞች የሚደክሙበትን የማዕድን ስራ በዘመናዊ የማጣራት እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የማረጋገጫ ሥርዓት በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡ አሰራሩ ዜጎችን ከሕገ-ወጥ ደላሎችና ከሀብት ብዝበዛም ይታደጋል።

በአጠቃላይ የቦሌ ለሚው የብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ የተፈጥሮ ሀብትን ከብክነት፣ ታታሪ ዜጎችን ደግሞ ከመጭበርበር በመታደግ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ በመደገፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

በልዩ እሸቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: