የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞዛምቢክ ጋር የሚያደርገውን ወሳኝ ጨዋታ ዛሬ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋል።
በምድብ 10 የተደለደለው ብሔራዊ ቡድኑ የማጣሪያ ውድድሩን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፎ መጀመሩ በብዙ መልኩ ተስፋ ሚያስቆርጥ ይመስል ነበር። በሱዳን እና ሴኔጋል በተመሳሳይ 1 ለ 0 የተረቱት ዋልያዎቹ፣ ከቀናት በፊት ሞዛምቢክን በማሸነፍ ተስፋቸውን አለምልመዋል።
በከነዓን ማርክነህ ግብ ማፑቶ ላይ 1 ለ 0 ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ የምድብ አራተኛ ጨዋታውን ዳግም ከሞዛምቢክ ጋር ያከናውናል።
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በመካከላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነት ያለ ሲሆን ሞዛምቢክ አራት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ሶስት ነጥብ መያዛቸው ጨዋታውን እንዲጠበቅ አድርጎታል።
በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማፑቶውን ድል በባሕር ዳር ከደገመ በስድስት ነጥብ የምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል።
ይህም ትናንት የምድቡ መሪ ሴኔጋል ሱዳንን መርታቷ፣ ዋልያው ከዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ካሳካ ከወራት በኋላም ሱዳንን ካሸነፈ ወደ አፍሪካ ዋናጫ የማለፍ እድሉን በእጅጉ ያሰፋል።
በዚህ ምክንያት ዛሬ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ትልቅ ክብደት ይኖረዋል።
የዛሬውን ጨምሮ መጋቢት ወር ላይ ከሱዳን እና ሴኔጋል ጋር የሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የብሔራዊ ቡድኑን ከስድስት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመመለስ እድል ይወስናሉ። ከዛ በፊት ትልቁ ፈተናን ዛሬ በባሕር ዳር ተፈትኖ ማለፍ ይጠበቅበታል።
የዛሬው ጨዋታ የመሃል ዳኛው ንፋሊ ጃርጁን ጨምሮ በጋምቢያውያን ዳኞች ይመራል።
በአብርሃም አድማሱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: