Search

ታዳጊ አትሌቶቻችን የኢትዮጵያን የድል ጉዞ የምታድሱ ሀገራዊ ኩራቶቻችን ናችሁ - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 116

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የ2026 የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ በአንደኝነት እንድታጠናቅቅ ያስቻሉ ታዳጊ አትሌቶችን በአካል አግኝተው አበረታተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አትሌቶቹ በአፍላ ዕድሜያቸው በዓለም መድረክ ባሳዩት ብቃትና ባስመዘገቡት ድል የሀገራቸውን ሰንደቅ በክብር ከፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ለመላው ኢትዮጵያውያን ደስታ እና ኩራት ለታዳጊው ትውልድ ደግሞ ታላቅ ተስፋ እና ተምሳሌት መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአሁኑ ድላቸው ለነገ የላቀ ስኬት መነሻና መሠረት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፣ አትሌቶቹ በራሳቸው በመተማመንና ህልማቸውን በማሳደግ ከዛሬው ድል የበለጠ ከፍታን እንዲያልሙ አሳስበዋል።

ለመጪዎቹ የዓለም ሻምፒዮናዎችና ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በበለጠ ብቃት፣ በትጋትና በቁርጠኝነት እንዲዘጋጁም መልዕክት አስተላልፈዋል።

መንግሥት በቀጣይ የስኬት ጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋገጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አትሌቶቹ ችሎታቸውን በቀጣይነት እያዳበሩ የሀገራቸውን ስምና ሰንደቅ በዓለም አደባባይ በተከታታይ ከፍ ለማድረግ በጽናት ለድል እንዲሰለፉ አደራ ብለዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: