Search

በአማራ ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከመስከረም 30 ጀምሮ ይሰጣል

ሰኞ መስከረም 26, 2018 70

በአማራ ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ለአራት ቀናት እንደሚሰጥ የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታውቋል፡፡
በክልሉ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች ለሆኑ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ክትባቱ እንደሚሰጥ የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የ3ኛ ዙር የተቀናጀ የፖልዮ ክትባት ዘመቻ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በባሕርዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በመድረኩ እንደገለጹት፤ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በሽታ ለዘላቂ የአካል ጉዳት እና ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡
በመሆኑም በትብብር የፀረ - ፖሊዮ ክትባት በመስጠት ሕጻናትን በመታደግ ጤናማና አምራች ትውልድ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
የፖሊዮ ወረርሽኝን በወቅቱ በፍጥነት መከላከል ካልተቻለ በሕፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ገልጸው፤ ይህን ለመከላከል የፀረ - ፖሊዮ ክትባት ዘመቻው በቤት ለቤት፣ በሕጻናት ማቆያ፣ በትምህርት ቤቶች እና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንደሚሠጥም ጠቁመዋል።
በክልሉ ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ለአራት ቀናት ለሚሰጠው የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካል የተቀናጀ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተስፋሁን ደስታ