በትናንትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ሰባተኛው ታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሥነሥርዓት ተካሂዷል።

በ2010 ዓመተ ምህረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው ይኽ ሥነ-ሥርዓት የዜግነት የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ እና በታማኝነት የሚፈፅሙ ዜጎችን ለማበረታታት ታቅዶ የሚተገበር ነው።

በዘንድሮው መርሐ ግብር 700 ታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፤ በ2017 ዓመተ ምህረት እንደነበራቸው አስተዋጽኦ መጠን 105 የፕላቲኒየም ደረጃ፣ 245 የወርቅ ደረጃ፣ 350 ደግሞ የብር ደረጃ ተሸላሚ ሆነዋል።

የጋራ አስተዋጽኦዋቸው በሥራ ዘመኑ 900.22 ቢሊዮን ብር በግብር እንዲሰበሰብ አስችሏል።
በተጨማሪም የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በግብር እና ቀረጥ አሰባሰብን ብቁ እና ግልፅ የሚያደርጉ የዲጂታል ሥርዓቶችን ማስጀመራቸውም ተገልጿል።

ከነዚህም ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት፣ ኤሌክትሮኒክ የጉምሩክ አስተዳደር ሥርዓት እና ኤሌክትሮኒክ የጭነት መከታተያ ሥርዓት እንደሚገኙበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
#ebcdotstream #PMOEthiopia #AbiyAhmed